የደቡብ ኦሞ ቴአትር ኩባንያ (ደኡቴኮ) መስራች አባል የሆነችው ጋዜጠኛ እና የፊልም ባለሞያ አሌክሳንድራ ጀኖቫ https://twitter.com/Alexandraaa_cg ባሳለፍነው ሳምንት እአአ ጥቅምት 26/2021 ዓ.ም በዩናይትድ ኪንግደም ከሚካሄደው “የጥቁር ህዝቦች ወር” ጋር በተያያዘ ‘መሬታችን’ የተሰኘ ዘጋቢ ፊልሟን አስመርቃለች። ፊልሙ በእንግሊዝ ሀገር የሚኖሩ ጥቁር አርሶ አደሮችን ታሪክ፣ ውጣ ውረድ፣ እና በነጮች የበላይነት ከሚመራው የግብርና ስርአት ጋር የሚያደርጉትን ትንቅንቅ ያስቃኘ ነው።
አሌክሳንድራ ባለፉት ጥቂት አመታት እንደ ህትመት ጋዜጠኝነቷ እና ፊልም ባለሞያነቷ በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ የምግብ እና ግብርና ታሪኮችን የትኩረት ማዕከሏ አድርጋ በመስራቷ በሀገሪቱ የግብርና ዘርፍ ውስጥ ያለውን የነጭ የበላይነት በጥልቀት የመረዳት እድል ገጥሟታል። በዚህም የጥቁሮችን መቋጫ የሌለው የሚመስል መከራ ለአለም ለማሳየት ቆርጣ መነሳቷን ታስረዳለች።
በእለቱ ፊልሙ ውስጥ በተካተቱት የእንግሊዝ ጥቁር ገበሬዎች ታሪክ መነሻነት በእለቱ ታዳሚ በነበሩ አካባቢያዊ አርሶ አደሮች፣ ፊልም ሰሪዎች፣ የማህበረሰብ መብት ተሟጋቾች፣ የፎቶግራፍ ባለሞያዎች፣ ህግ አውጪዎች እና ሌሎች ተጋባዦች ዘንድ እንግሊዝ ውስጥ ስላለው የመሬት አስተዳደር እና በተለይም ጀማይካዊያን ወጣቶችን እንዴት ባለ ስልት ከስርአቱ ውጪ እንዲሆኑ ስለመደረጉ ጠለቅ ያሉ ሀሳቦች ተነስተዋል።
በውይይቶቹም የፊልሙ ዳይሬክተር አሌክሳንድራ “እንግሊዝ ውስጥ የጥቂት (ምናልባትም ከአጠቃላይ የእንግሊዝ ህዝብ ከአንድ በመቶ በታች የሚሆኑት) ነጭ የከፍተኛው መደብ አባላት የመሬት ባላባትነት በታሪክ እና በስነ ህዝብ ጥናት ተደግፎ ለዘመናት ኖሯል። ‘መሬታችን’ ፊልምም በእንግሊዝ የግብርና ታሪክ ውስጥ ስር የሰደደውን ኢ-ፍትሀዊነት ብቻ ሳይሆን በፊልሙ ውስጥ በተካተቱት አርሶ አደሮች ጠንካራ መንፈስ እና አልበገር ባይነት እያደገ ያለውን የሀገሪቱን የግብርና ኢንዱስትሪም ጭምር ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ አምናለሁ” ስትል ሀሳቧን ለታዳሚዎቹ አጋርታለች። አሌክሳንድራ አክላም “ይህ ዘጋቢ ፊልም ሀገሪቱ ውስጥ ባለው አድሎአዊ አሰራር ተስፋ በመቁረጥ ‘ግብርና ለ’ኔ አይሆነኝም’ ብለው ለተቀመጡ ሰዎችም መነሳሳትን እንደሚፈጥር ተስፋ አደርጋለሁ” ብላለች።
‘መሬታችን’ ፊልምን ከጥቁር ህዝቦች ወር ጋር በተያያዘ በአይ ቲ ቪ ለተወሰኑ ግዜያት በሚከተለው ድረ ገፅ መመልከት ይቻላል፡ https://www.itv.com/hub/black-british-and-breaking-boundaries/10a1969a0002
ፎቶ፡ በሎክስሌይ ሳሙዳ
Comments