ጤና ይስጥልኝ ውድ አንባቢዎቼ። ‘ትምህርት ለሁሉም’ በሚለው ምጥን ፅሁፍ (https://www.southomotheatre.com/post/%E1%89%B5%E1%88%9D%E1%88%85%E1%88%AD%E1%89%B5-%E1%88%88%E1%88%81%E1%88%89%E1%88%9D) እንዳወጋኋችሁ ከፊል አርብቶ አደሩ ኦሊሰራሊ ኦሊቡዪ የትምህርትን ጥቅም ተረድቶ ህዝቡን ለማስተማር እና ከጭለማ ጉዞ ለማላቀቅ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ እያደረገ ነው። ምስጋና ጆሮዋቸውን ለሰጡት የአውስትራሊያ፣ አሜሪካ እና እንግሊዝ ጎብኚዎች ይሁንና ጥረቱ ፍሬ የሚያፈራበት ቀን የቀረበ ይመስላል። በነገራችን ላይ ኦሊ በጣም ፈጣን እና አስተዋይ ሰው ነው። ከፊት ለፊቱ ያለውን እድል እንዴት አድርጎ መጠቀም እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል። በአለማችን ያሉ ስኬታማ ሰዎች ‘የስኬት ምንጭ እድል ሲደመር ብርቱ ጥረት’ መሆኑን በብዛት ሲያስተምሩ ይደመጣል እኔም የሀሳባቸውን ትክክለኝነት በኦሊ አረጋግጫለሁ። ኦሊ በማንኛውም አጋጣሚ የሚያገኘውን እድል በብርቱ ጥረቱ ወደ ውጤት የመቀየር አቅም አለው። ‘እድል አንዴ ነው’ እንዲል የሀገሬ ሰው እንደአብዛኛዎቻችን ‘ምክንያት’ በማብዛት የቀረበለትን እድል አሳልፎ አይሰጥም በዚህም ከብሄረሰቡ ባህርን ተሻግሮ እውቀት ቀስሞ የተመለሰ የመጀመሪያው ሰው ለመሆን በቅቷል። ከአውስትራሊያ ሚሲዮናዊያን ጋር በመሆን ለሁለት አመታት ወደ አውስትራሊያ አቅንቶ የእንግሊዝኛ ቋንቋን ተምሮ ተመልሷል። ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰም በኋላ እውቀቱን ለብቻው አድርጎ አልተቀመጠም። ወንድሙን እና ሌሎች ከጎብኚዎች ጋር የሚሰሩ የሀገሩን ልጆች አስተምሯል። የመምህር ብቃት የሚለካው በተማሪዎቹ ውጤት ነውና ሚሊሻ (የኦሊ ወንድም) እንግሊዝኛ ሲናገር የተመለከተ ኦሊ ምን አይነት ድንቅ አስተማሪ መሆኑን መረዳት ይችላል። ሚሊሻ እንኳን ባህር ሊሻገር ከጂንካ አልፎ አያውቅም ነገር ግን ከአንዳንድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ እና ስነፅሁፍ ዲግሪ ከጫኑ የዘመናችን ምሁሮች እጅግ የላቀ የቋንቋ ክህሎት አዳብሯል። ያለምንም የትምህርት መርጃ መሳሪያ እና ያለምንም መሰረተ ልማት እውቀትን እንዲህ መቀበል የሚችል ማህበረሰብ በአግባቡ ቢማር የት ሊደርስ እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ኦሊ እውቀት ማሳደዱን በዚህ አላበቃም። ከሌሎች አሜሪካዊያን ጋር በመተባበር ደግሞ በቀደመው ፅሁፍ እንደተመለከተው ስዕላዊ የመማሪያ መፅሀፍ በሙርሲ፣ በአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ፅፎ አሳትሟል። ለቴክኖሎጂ ልዩ ፍቅር ያለው ኦሊ በካሜራ ጥበብ በመማረክ ከጎብኚዎች በዳረጎት በሚያገኛቸው ያረጁ ካሜራዎች ስለፊልም አቀራርፅ በቂ ሊባል በሚችል ደረጃ እራሱን ካስተማረ በኋላ መቀመጫውን ለንደን፣ ዩናይትድ ኪንግደም ካደረገው የ ‘ያንግ ኤንድ ያንግ ፊልም ፕሮዳክሽን’ (https://www.youngandyoung.co.uk/ ) ባለቤት አቶ ቤን ያንግ (https://uk.linkedin.com/in/ben-young-61762b4 ) ጋር የተፈጠረለትን የትውውቅ አጋጣሚ በመጠቀም በስምንት አለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ እጩ የሆነ፣ በሁለቱ ላይ ደግሞ በአሸናፊነት የተመረጠ “ሹቲንግ ዊዝ ሙርሲ” (http://www.shootingwithmursi.com/ ) የተባለ ዘጋቢ ፊልም ሰርቶ አለምን ጉድ አሰኝቷል። ከዚህ ፊልም ስኬት በኋላም ኦሊ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በካናዳ እንዲሁም አውስትራሊያ በማቅናት ህልሙን፣ ፊልሙን፣ ህዝቡን እና ሀገሩን አስተዋውቋል።
ኦሊ በየጊዜው በጎብኚዎች እና በመንግስት ጫና እየተሸረሸረ እና እየተሸቀጠ የመጣው ባህሉ እጣ ፈንታ ያሳስበው ጀመር። በዚሁ ከቀጠለ ምናልባት የልጆቹ፣ ግፋ ቢል የልጅ ልጆቹ የማንነት መሰረት እንደሚናጋ አመነ። ቢቻል ከዘመን ቀድሞ ካልሆነም ከዘመን ጋር አብሮ መራመድን መርሁ አድርጎ የሚኖረው ኦሊ ባህሉን በዘላቂነት ለማስቀመጥ፣ ለተተኪው ትውልድም ያልተበረዘ ማንነት ለሚያስተላለፍ፣ እንዲሁም ለቀሪው አለም የሙርሲን ድብቅ ሀብቶች በተገቢው መልኩ በማሳየት ለሙርሲ ድምፅ ለመሆን፣ ኢትዮጵያንም ባልታየ መነፅር ለማሳየት አልመ። እድልና ትጋት የማይለዩት ኦሊ ይህንን ሀሳቡን ይዞ ከአስር አመታት በፊት አለም አቀፍ ተሸላሚ ፊልም (https://www.youtube.com/watch?v=gxDarLoEeaA ) አብሮት የሰራው አቶ ቤን ያንግ ጋር በመደወል እንቅልፍ የነሳውን የሀገሬውን የማንነት መሸርሸር ያጫውተዋል። አቶ ቤንም በአካባቢው ያሉ በምርምር፣ በፊልም፣ በቴአትር፣ እና በሚዲያ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሞያዎችን ሰብስቦ በኦሊ መሪነት የሙርሲን እውነተኛ ገፅታ እንዲሁም ኢትዮጵያን ባልታየችው መነፅር ሊያሳይ የሚችል የምርምር፣ የቴአትር አቅርቦት እና የዘጋቢ ፊልም ፕሮጀክት ነደፈ። ንድፉም በ”ዩኒቨርሲቲ ኦቭ ለንደን፤ ስኩል ኦቭ ኦሪየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ” (https://www.soas.ac.uk/ ) ተቀባይነት አግኝቶ የተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ ተደረገለት (https://grnpp.org/olisarali/ )። ኢትዮጵያዊያን እና ምዕራባዊያን ምሁራንን ያካተተው ይህ አዲስ ስብስብ (https://www.southomotheatre.com/meet-the-team ) የኦሊን ህልም ተጋርቶ ግቡን ከዳር ለማድረስ ታጥቆ ተነሳ። የመጀመሪያው ተግባር ታዲያ ኦሊን ሊሰራ ከታቀደው ነገር ጋር ማስተዋወቅ ነበር። ኦሊ ምንም እንኳን የዘጋቢ ፊልም እና የምርምር አሰራር ልምድ ቢኖረውም ቴአትር ስለሚባለው ፅንሰ ሀሳብ ግን ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። ቴአትር ሲባል ሰምቶም አይቶም አያውቅም። ስለዚህ ቀጣዩ የቤት ስራ በተግባር የቴአትርን ምንነት ማሳየት እና በአጭር የስልጠና መርሀ ግብር ኦሊን ከቴአትር ፅህፈት እና ትወና ጋር ማስተዋወቅ ነው። ለዚህ ስኬትም በቅድሚያ በመዲናችን አዲስ አበባ የሚገኙ ቴአትር ቤቶችን ማስጎብኘት እና የተወሰኑ ትውፊታዊ ቴአትሮችን እንዲመለከት በማድረግ ከጥበቡ ጋር እንዲተዋወቅ ተደረገ። በመቀጠልም በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የቴአትር ጥበብን የሚያስተምሩ ምሁራን አባል የሆኑበት የአዲሱ የባህል ፕሮጀክት ሁነኛ የቴአትር ማሰልጠኛ ፍልጋ መስፈርቶችን አውጥቶ መፈተሽ ጀመረ። ቀዳሚ ምርጫውም በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ታሪክ ለሁለት ጊዜ በተከታታይ አለም አቀፍ የቴአትር ቀንን በማክበር በ100 አመት የኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የቴአትር ባለሞያዎችን ከአማተር እስከ ፕሮፌሽናል በማሰባሰብ፣ በቴአትር ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርቦት የቴአትርን ሞያ ሳይንሳዊነት በማረጋገጥ፣ የተለያዩ የቴአትር ዘርፍ ባለሞያዎች ከመላው ሀገሪቱ ተሰባስበው ከምንም አይነት ጫና በፀዳ መልኩ ስለ ሞያቸው የመከሩበት እና የተዋወቁበት እንዲሁም በአካዳሚ አለም ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና የተሰጠበት መድረክ በማዘጋጀት፣ ኢትዮጵያን በተባበሩት መንግስታትድርጅት የምጣኔ ሀብት፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ ድርጅት ስር የሚገኘው የአለም የቴአትር ተቋም አባል ለማድረግ እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ የቴአትር ማዕከልን ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ ያለው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ (https://www.facebook.com/wku.edu.et / www.wku.edu.et ) ነበር።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በጥበብ የተዋጀ አመራር፣ በትንታግ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህራን እና ተማሪዎች ድጋፍ “ጎበዝ አዘጋጅ መንገደኛን ጠርቶ ብቁ ተዋናይ ማድረግ የሚችል ነው” እንዲል ብሂሉ ሰለ ቴአትር ጥበብ ምንም እውቀት የሌለውን ኦሊን የማወቅ ፍላጎት እና የመረዳት ፍጥነት ብቻ በመጠቀም በጥቂት ቀናት ውስጥ በቴአትር መንፈስ የማጥመቁ ስራ ተጀመረ። ድካሙ ከልብ፣ ፍላጎቱ ከአንጀት፣ ቅንጅቱ የተሳካ ነበርና ኦሊ ወልቂጤ በቆየባቸው ጥቂት ቀናት በውስጡ ታምቆ ያለውን ቱባ ታሪክ እንዴት በቴአትር መልክ መፃፍ እንደሚችል እንዲሁም ስለ ትወና ምንነት እጅግ መሰረታዊ የሆኑ ክህሎቶችን ተምሮ፣ አለም የዞረበትን ዘጋቢ ፊልምም በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር አሳይቶ ትልቅ የስኬት መንፈስ ተላብሶ ወደ ሙርሲ ምድር ተመለሰ።
እግረ መንገዱንም ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በወፍ በረር ስለ ሙርሲ ህዝብ ያላቸውን ግንዛቤ ጠየቀ። ምላሹ ይህ ነበር፡ https://www.youtube.com/watch?v=FTG-Aa-vrdM
ኦሊ ወደ ሙርሲ ከተመለሰ በኋላ ከፀሀፊ ተውኔት፣ አዘጋጅ እና የቴአትር ጥበብ መምህር ተስፋሁን ሀዲስ ጋር በመሆን “ቲራኒያ ኮ ኮይሳኒ” ወደ አማርኛው ሲመለስ “ዳኛው” በሚል ርዕስ በሙርሲ ብሄረሰብ የማንነት መሰረቶች ላይ የሚያጠነጥን የ”መልቲሚዲያ ቴአትር” ቅርፅን የያዘ ተውኔት መፃፍ ጀመረ። የቴአትር አቅርቦቱ የሙርሲን ታሪክ ስለ ትወና የላቀ እውቀት በሌላቸው የሙርሲ ብሄረሰብ ተዋንያን በማስተወን፣ በሀገረ እንግሊዝ የሚገኝን የ”መልቲ ሚዲያ” ቴክኖሎጂ በመጠቀም በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ ያልተሞከረ ቅርፅ እና ይዘት ያለው አዲስ አቀራረብ ማሳየትን አልሟል። ይህ በሀምሌ ወር መጨረሻ ለእይታ ለመብቃት እየተሰናዳ ያለው ቴአትር ኢትዮጵያዊ የቴአትር ቅርፅን ለመፈለግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ በምሁራን ዘንድ ታምኖበታል። ለስኬቱም የሁሉንም ድጋፍ እየጠየቅሁ የዝግጅቱን ሂደት በተከታታይ እንደማስነብባችሁ ቃል እገባለሁ። ለዛሬው በዚሁ ልሰናበት። ቸር ይግጠመን።
ስለ ፕሮጀክቱ በዝርዝር ለመረዳት ከፈለጉ የሚከተሉትን ማህበራዊ ገፆች ይጎብኙ፡
Comments