top of page
Search
southomotheatre

የሁለት አንበሶች ወግ

Updated: Nov 22, 2021


አስገምጋሚ ድምፁ ከስምንት ኪሎሜትር ርቀት የሚሰማው የአውሬዎች ሁሉ ንጉስ፣ ለማንም የማያጎነብሰው ታላቁ የድመት ዘር ለዘመናት የሀገራችን ኢትዮጵያ መለያ ምልክት ሆኖ ኖሯል። ይህ የታላቅነት እና የአሸናፊነት ምሳሌ ታላቋ ብሪታኒያን፣ ጎረቤታችንን ኬንያን፣ ቅኝ ባለመገዛት የያዝነውን የእምቢ ባይነት መንበር የምትጋራንን ላይቤሪያን፣ በቅንጡ አኗኗሯ የምትታወቀውን ሉክዘምበርግን፣ በእድገቷና ለሰው ልጆች ኑሮ አመቺ በመሆኗ ወደር የማይገኝላትን ሲንጋፖርን እና ሌሎች ጥቂት የአለም ሀገራትን ወክሎ የትውልዶቻቸው መቅረጫ፣ የማንነታቸው ማሳያ፣ እና የኩራታቸው ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። ይህ ሀገራት በታሪክ አሊያም በስልጣኔ የበላይነታቸውን እና ለጠላት አልምበረከክ ባይነታቻውን ያለ ቃላት ጋጋታ የሚገልፁበት የአሸናፊነት ምልክት ለየትኛውም እንስሳ፣ ለማንኛውም ጠላት አያጎነብስም።

የኢትዮጵያን ድንበር ለዘመናት በቀስት እና ዱላ ብቻ ሲያስከብር የኖረው የኢትዮጵያ አንበሳ፣ የኢትዮጵያን መሬት ለባዕድ ማዳበሪያ ሳያጋልጥ በሀገር በቀል እውቀቱ እየተመራ ለበርካታ መቶ አመታት ለምነቱን አስጠብቆ ያቆየው የሀገሬ አንበሳ፣ በሀገር በቀል እውቀቱ መድሀኒቱን፣ የጠፈር ምርምሩን፣ የተፈጥሮ ምስጢራትን ሲተነትን የኖረው ኢትዮጵያዊ አንበሳ፣ በባህሉ መሰረት ትዳር ለማግኘት፣ የማህበረሰቡን ይሁንታ ለመጎናፀፍ የሰው አንበሳነቱን ለማረጋገጥ ምንም የማይገድበው የሙርሲ ጀግና፣ ለየትኛውም ድንበር ተሻጋሪ ጠላት፣ ለየትኛውም ድርቅ እና ረሀብ፣ ለየትኛውም መከራና ችግር፣ ምድራዊ ለሆነ ምንም ነገር አያጎነብስም፣ አይንበረከክም።

ያለማጎንበሱ ሚስጥር ከመታበይ አሊያም ከማን አለብኝነት የመነጨ ሳይሆን ለምሳሌ አንድ ወታደርን ብንወስድ፤ ወታደር አጎነበሰ ወይ ደግሞ መሳሪያውን ዘቅዝቆ አስጎነበሰ ማለት ግላዊ ሽንፈቱን ብቻ ሳይሆን ይዞት የተነሳው ሀሳብ፣ ከጀርባው ያለው ሀገር፣ የሚቆምለት፣ የሚታገልለት፣ የሚሞትለት አላማ አጎነበሰ ማለት ነው። ስለዚህ በሀገር እና ወገን ጉዳይ ማጎንበስ ማለት አንድ ጊዜ ሳይሆን በተደጋጋሚ መሞት ማለት ነው። ይህ ኢትዮጵያዊ ጀግናም ገና ለማጎንበስ ሲያስብ በጀርባው ያዘላቸውን የማንነት ሀላፊነቶች ያስባቸዋል። በዚህ ግዜ ታዲያ ተንበርክኮ ሁለት ጊዜ ከሚሞት ልክ እንደ ቅድመ አያቱ ቴዎድሮስ በቁሙ ታግሎ መራራዋን ፅዋ መጋትን ይመርጣል።

የአንበሳውም ሆነ የሙርሲው ኢትዮጵያዊው ጀግና ሀያልነት ግን በምድራዊያን ላይ ብቻ የተወሰነ ነው። ከሰማያዊው ፈጣሪ የሚያገኟቸውን ገፀ በረከቶች በፍፁም ትህትና እና መተናነስ እንዴት አድርገው መቀበል እንዳለባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። በጉልበታቸው የማይወሰነውን፣ በአቀራረባቸው የማይበረግገውን፣ በቁጣቸው የማይርደውን ሀያል ተፈጥሮ ዝቅ ብለው፣ ተንበርክከው ይቀበላሉ። ልክ በሌሎቹ ላይ የበላይ እንደሆኑት ሁሉ በውሀም ላይ ልሰልጥን ቢሉ፤ ውሀ ሽቅብ አይፈስምና ህልማቸው ቅዠት ሆኖ በጥም ባለቁ ነበር።

ሁሉም ፍጡር የሚፈልገውን ለማግኘት ዝቅ ይላል፣ ይንበረከካል!

12 views0 comments

Comments


bottom of page