top of page
Search
  • mastu89

የአርበኞች ማስታወሻ

ክቡራን የደቡብ ኦሞ ቴአትር ኩባንያ ምጥን የኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ አንባቢዎች እንደምን ከርማችኋል? ዛሬ መቀመጫውን በመናገሻችን መሀል ፒያሳ ከሚኒሊክ አደባባይ እና የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን አባት ከሆኑት ሰማእቱ አቡነ ጴጥሮስ አደባባይ መሀል በተለምዶ ማዘጋጃ ቤት እየተባለ በሚጠራው የከተማው አስተዳደር ዋና ህንፃ ውስጥ ያደረገውን የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ አመሰራረትን በወፍ በረር አስቃኛችኋለሁ።

ለዚህች ምጥን ዋቢ የሆነኝ ፅሁፍ በማን እንደተፃፈ የሚገልፅ መረጃ ማግኘት አልቻልኩም ሆኖም የተፃፉት መረጃዎች ትክክለኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የተለያዩ አባሪዎችን እና ግለሰቦችን አዋይቻለሁ። ይህ በኢትዮጵያ ቴአትር የአንድ መቶ አመት ታሪክ ውስጥ በፊታውራሪነት የሚጠቀሰው ቴአትር ቤት የተቋቋመው ልክ እንደ ሀገር ፍቅር ቴአትር (https://www.southomotheatre.com/post/%E1%8B%A8%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%88%80%E1%8C%88%E1%88%AD-%E1%8D%8D%E1%89%85%E1%88%AD-%E1%88%9B%E1%88%85%E1%89%A0%E1%88%AD--%E1%88%80%E1%8C%88%E1%88%AD-%E1%8D%8D%E1%89%85%E1%88%AD-%E1%89%B4%E1%8A%A0%E1%89%B5%E1%88%AD) ኢትዮጵያዊያንን ስለ ሀገር ፍቅር በመስበክ ሁሉም ህዝብ ሀገሪቱን ከጠላት ወረራ እንዲታደግ ለማነሳሳት ባይሆንም የሀገርን ክብር በደም እና አጥንታቸው ፍላጭ ያስከበሩ ጀግኖችን ስም ከመቃብር በላይ ማዋልን አላማው አድርጎ ነበር። ሁለቱም ቴአትር ቤቶች ስለሀገር ፍቅር እና ክብር ማስታወሻነት የተቋቋሙ በመሆናቸው ከቴአትር አገልግሎታቸው በተጨማሪ የሀገር ባለውለታነታቸው ጎልቶ ይታያል። የዚህ ድንቅ ሀሳብ ቆስቋሽ እና መሪ ገና በ18 አመቱ በእድሜ እና በጥበብ አንጋፎች ብቻ የሚቀዳጁትን የ’ቀኝ ጌታ’ነት ማዕረግን ያገኘው አንጋፋው አርበኛ፣ ባለቅኔ፣ ገጣሚ፣ ደራሲ’ና፣ የቴአትር ባለሞያ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ነበር። ዮፍታሄ ‘የጀግኖች አርበኞችን ስም ከመቃብር በላይ ለማዋል የሚያስችል የቴአትር ማህበር በጀግኖች አርበኞች ማህበር ፅ/ቤት ስር ሆኖ የሚተዳደረው ግን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እንዲሆን’ ሲል ያቀረበው ሀሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ነሀሴ 19/1939 ዓ.ም በሀገራችን የመጀመሪያው ‘የቴአትር ማስፋፊያ ፅ/ቤት’ ተቋቋመ።

አራት ኪሎ መቀመጫውን ያደረገው የቴአትር ማስፋፊያ ፅ/ቤት የቴአትር፣ ዳንስ እና ውዝዋዜ ጥበባትን በተጠሙ ትንታግ የኢትዮጵያ ልጆች ይመራ ነበርና ገና የመቋቋሚያ ብስራት ዜናው እንደተነገረ “መቀነቷን ትፍታ” የተሰኘውን ቴአትር በሚያስገርም ፍጥነት አስጠንቶ ለመድረክ አበቃ። ቡድኑም ስሙ እየገነነ እና ስራዎቹም እየተወደዱ ሲመጡ ከተቋቋመ ገና በአንድ አመቱ በ1940 ዓ.ም መቀመጫውን ከአራት ኪሎው የጀግኖች አርበኞች ማህበር ፅ/ቤት ወደ ፒያሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ወዳለው የአዲስ አበባ አውራጃ ፅ/ቤት ቀየረ። በወቅቱ በነበሩ የመንግስት አካላት እንዲሁም ተመልካቾች አድናቆትን ያተረፈው የቴአትር ቡድን ‘የሚደረግልኝ ጭብጨባ እና የማገኘው ገቢ አልተመጣጠነልኝም’ የሚሉ አባላቱ ድምፅ እየረበሸው መጣ። የቡድኑ አባላት የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ ሀላፊዎቹን በእጅጉ አስጨነቀ። ጥያቄው የቢሮ አሰራሩን ተከትሎ ወደ ማዘጋጃ ቤት ሀላፊዎች ቢቀርብም ይህ ነው የሚባል ምላሽ ሳያገኝ ቀረ። በስተመጨረሻም አስተዳደሩ የቴአትር ቡድኑን መበተንን በአማራጭነት ወሰደ። የተቋቋመለትን አላማ በበቂ ሁኔታ ከግብ ሳያደርስ የቴአትር ማስፋፊያ ፅ/ቤቱ ከጥቂት ብልጭታ በኋላ ከሰመ። ከቡድኑ መበተን በኋላ አባላቱ ቢያንስ ለስምንት አመታት ያክል በተለያየ ቦታ ተበታትነው ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ በ1948 ዓ.ም የቀዳማዊ ሀይለስላሴ ቴአትር ቤት (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር) ሲመሰረት አባላቱ በድጋሚ ተሰብስበው በአዲሱ ቴአትር ቤት በአዲስ መዋቅር የመስራት እድል እንዲያገኙ ተደረገ።

በቡድኑ አባላት አለመስማማት እና በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ቴአትር ቤት መመስረት በቀላሉ ማንሰራራት ያልቻለው የማዘጋጃ ቤት ቴአትር ክፍል በ1958 ዓ.ም በማዘጋጃ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ወርቁ አማካኝነት በድጋሚ ህይወት ዘራ። አቶ ታደሰ የወቅቱን ከንቲባ ቢትወደድ ዘውዴ ገ/ህይወትን በተቋማቸው ስር የሚመራ የሙዚቃ ቡድን መመስረት የሚኖረውን ፋይዳ በጥልቀት ከማስረዳት በተጨማሪ የአመሰራረት ሙሉ ሰነዱን በማዘጋጅት ካሳመኑ በኋላ በ1959 ዓ.ም የአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ እንደ አዲስ ተሞሽሮ ብቅ አለ። ቴአትር ቤቱ ሲመሰረት አንጋፋውን የአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ አርማ የሆነውን ፋንቱ ማንዶዬን ጨምሮ 10 ሴቶችንና 50 ወንዶችን መልምሎ ለአንድ አመት ያህል ስልጠና ከሰጠ በኋላ በ1960 ዓ.ም በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ገባ። የሙዚቃና ቴአትር ክፍሉ በአቶ ተፈራ አቡነወልድ የሙዚቃ ክፍል ሀላፊነትና አቀናባሪነት እንዲሁም በአቶ ለማ ገብረህይወት የባህል ሙዚቃ አሰልጣኝነት የሙዚቃ ስራውን በአሁኑ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ግቢ ውስጥ ጀመረ። አቶ ሳህሉ እዝነህ ደግሞ የቀልዶች እና አጫጭር ቴአትሮች አሰልጣኝ ተደርገው ስራቸውን በማዘጋጃው አዳራሽ ውስጥ ቀጠሉ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ መልክ ተቀይሮ ሀገሪቱ ከንጉሳዊ አገዛዝ ወደ ወታደራዊ መንግስት በተሸጋገረችበት በ1967 ዓ.ም የአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽም የለውጡ ተጠቃሚ በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ስር ነቀል እድሳት እና ቋሚ ስራ አስኪያጅ ተመድቦለት በሞግዚት ከመተዳደር ነፃ ወጣ። የመጀመሪያው ስራ አስኪያጅም አቶ ተፈሪ ብዙአየሁ ተደርገው ተሾሙ። አቶ ተፈሪ የአብዬ መንግስቱን ‘ባለካባ’ና ባለዳባ’ን አዘጋጅተው ለመድረክ ከማብቃታቸው በተጨማሪ 27 አዳዲስ ቅጥሮችን በማስፈቀድ የሙዚቃ እና የቴአትር ክፍሉን በሚገባ እንዳደራጁት ስለሳቸው የተፃፈው ስራቸው ምስክር ነው።

ቴአትር ቤቱ የበርካታ አንጋፋ እና ጀማሪ ፀሀፊያንና አዘጋጆች ስራዎችን ለመድረክ አብቅቷል። ቴአትር ቤቱ በቀደመ ዘመኑ እንደ “እሳት ሲነድ”፣ “የመንታ እናት”፣ “አቡጊዳ”፣ “መልዕክተ ወዛደር”፣ “መቅድም”፣ “ኦቴሎ”፣ “ቴዎድሮስ”፣ “ዕዝለ ጥበባት”፣ “ጤና ያጣ ፍቅር”፣ “ቅደሚ እግሬ”፣ “እመሪ ቤቴ”፣ “የጠላ ሻጭ ልጅ”፣ “የት ሄደሽ ነበር”፣ “የአዲስ አበባ ኮረዳ”፣ “መቃብር ቆፋሪ”፣ “የሲስትሮ ኦፔራ”፣ “ያላቻ ጋብቻ”፣ “ጁሊየስ ቄሳር”፣ “ስመኝ ስንታየሁ”፣ “ወጥመድ”፣ “የሚተኑ አበቦች”፣ “የከርቸሌው ዘፋኝ”፣ “የመጨረሻው ህልም”፣ “ቆንጆዎቹ”፣ “ዳና”፣ “ጣይቱ”፣ እና “የተረሳው እዳ” የመሳሰሉ ተውኔቶችን ለእይታ አብቅቷል።

ከቴአትር አቅርቦት በተጨማሪ አዳራሹን ለፊልም እይታ እያከራየ ገቢውን የሚያጠናክረው ቴአትር ቤት እንደ አበባ ሀ/ሚካኤል፣ ፋንቱ ማንዶዬ፣ መላኩ አሻግሬ፣ በሀይሉ መንገሻ፣ ጀማነሽ ሰለሞን፣ መዝሙር ተፈራ፣ አላዛር ሳሙኤል፣ ታምራት ምህረተአብ፣ ንጉሱ ብርሀኑ፣ ተስፋዬ ሀይሌ፣ አልማዝ ልመንህ፣ ዳናኤል ሙሉነህ፣ ጌታሁን ሀይሉ፣ ሳሙኤል ነጋሽ፣ ያምሮት ንጉሴ፣ ጌታቸው ታረቀኝ፣ ቶማስ ቶራ፣ ኩራባቸው ደነቀ፣ ፈለቀ ጣሴ ያሉ አንጋፋ አርቲስቶችን በሀላፊነት፣ በአዘጋጅነት፣ በተዋናይነት፣ በፀሀፌ ተውኔትነት እና በሌሎች የቴአትር ዘርፎች አቅፎ ሲሰራ የኖረ አንጋፋ የጥበብ ቤት ነው። በቴአትር ቤቱ ታሪክ ውስጥ በስፋት ስለሚነገረው የፀጋዬ እና የአባተ ዘመን በሌላ ምጥን አወጋችኋለሁ ለአሁኑ ግን በዚሁ ልሰናበት ቸር ይግጠመን።

Addis Ababa City Municipality


The New 'Mazegaja Theatre' Lobby

59 views0 comments

Comments


bottom of page