top of page
Search
  • mastu89

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ... ባልታየው መነፅር

ወድ የኢትዮጵያ ልጆች እንደምን ከርማችኋል? ዛሬ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ከገነቧት ሰበዞች መካከል ስለ አንዱ አሰፋፈር እጅግ በአጭሩ አወጋችኋለሁ። መልካም ንባብ።

የሰው ልጅ ታሪክ ከቅድመ ታሪክ አንስቶ የሰው ልጅ ፊደል ቀርፆ፣ የስዕል ጥበብን ፈጥሮ ታሪኩን ሰንዶ ማስቀመጥ እስከጀመረበት፣ የተሰነደውም ታሪክ እንደ አሰናጁ ፍላጎት ተጠምዝዞ ገሚሱ የፍቅር ቀሪው ደግሞ የጥላቻ እርሾ ተነስንሶበት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ እዚህ ደርሰናል። የኢትዮጵያ ታሪክም አንድ ግዜ ከየመን ሌላ ጊዜ ደግሞ ከማደጋስካር እየተነሳ የተለያዩ የማንነት ጥያቄዎችን እና የታሪክ ሽሚያዎችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። የኢትዮጵያዊያን የዘር ሀረግ ሲሻው ከአንድ ምንጭ ሲቀዳ ሲለው ደግሞ በአሉባልተኛ ‘የታሪክ ተመራማሪዎች’ ድፍየና ሲተረተር ዛሬ ላይ ቆመናል። ነገስታቶቻችን በአንዱ ሲሞካሹ በሌላው እየተወገዙ ተምረን የምናስተምረው ታሪክ ተደበላልቆብን የእውር ድንብራችንን እየተጓዝን አለን። የሆነው ሆኖ በክፉም ይሰነድ በበጎ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ከአፍሪካው ንጉስ እምዬ ምኒሊክ ዘመን የሚጀምር ለመሆኑ ግን የሚያጠራጥረን ምንም አይነት ሰነድ የለም። የ3000 ዘመን ታሪክ አለን ብለን ብንደሰኩር፣ “በፍፁም ታሪካችንማ የ5000 ዘመን ነው፤ ምስክራችንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ናት” ብለን ጉንጫችን እስኪዝል ብንከራከርም አዲሲቷ ኢትዮጵያ፣ ሉአላዊ ድንበሯ ተከብሮ ዛሬ ያለውን (በርግጥ ዛሬ ሳይሆን ኤርትራ ከመገንጠሏ በፊት) ቅርፅ ይዞ እኛም ‘ድንበራችን’ ብለን የምንጠብቀው ምድር የተሰራው በእምዬ ምኒሊክ አስተዳደር ነው።

ከላይ የጠቀስኳቸው በሰናጆቻቸው የእውነት መንገዳቸው የተሰመረላቸው የታሪክ መዛግብቶቻችን እንደሚሉት እምዬ ምኒሊክ በምስራቅ የሀረር ኢሚሬቱን (አርሲን ጠቅልሎ ያስተዳድር የነበረውን) የኢሚር አብዱላሂን፣ በደቡብ የካዎ ጦናን፣ የጋኪ ሰሪቾን፣ በደቡብ ምዕራብ የአጋዝ ዳርሳሞን፣ የአባ ጂፋርን፣ እንዲሁም የሌሎች በአሁኗ ኢትዮጵያ የመሬት ክልል ውስጥ የነበሩ ራስ ገዝ አስተዳደሮችን ብርቱ ክንዶች ጠምዝዘው ካስገበሩ በኋላ ከዘመነ መሳፍንት ፍትጊያ፣ ከአፄ ቴዎድሮስ ገድል፣ ከአፄ ዮሀንስ ውንጀላዎች፣ ከደጃች ጉግሳ የጣሊያን ገባርነት፣ ከንጉስ ሚካኤል ሽፍትነት የተረፈችውን ሰሜን ኢትዮጵያን ቀላቅለው ዛሬ ኢትዮጵያ የምንላትን የድንበር ወሰን ያላትን ሀገር ሰሩልን። በዘመኑ የነበሩ የአለም መንግስታት ግዛታቸውን በማስፋፋት የሀብት ምንጫቸውን ለማዳበር እና በሰው ልጅ ላይ ያላቸውን መሰልጠን ለማሳየት በሚያደርጉት ብርቱ የሞት የሽረት ትግል ውስጥ በጣም ብዙ ለንግግርም ለፅሁፍም የማይመቹ ግፎችን ፈፅመው አልፈዋል። “በእንግሊዝ ፀሀይ አትጠልቅም” እስኪባል ድረስ ግማሽ አለምን ገዝተው ሲያስገብሩ በየቦታው ያሉ ህዝቦች ‘እንኳን ደህና መጣችሁ’ እያሉ የዘንባባ ዝንጣፊ እያነጠፉ አልተቀበሏቸውም። ይልቁንም እየሞቱ፣ እየታረዱ፣ እየተቀጠቀጡ ከአቅማቸው እጅግ በገዘፈ ሁኔታ ለመጣባቸው ወራሪ ተገዝተው ለመኖር ተገደዋል። ዛሬ ታዲያ ሰው ሆነው እንደ ቁስ፣ የስላሴ ፍጥረት ሆነው ሳለ የሰው ልጆች (የእንግሊዝ ቀይ ለባሾች) ጠፍጥፈው የሰሯቸው ይመስል መለያ ተሰጥቷቸው “የእንግሊዝ ንብረቶች” ተብለው በመላው አለም ተሰራጭተው የሚኖሩ በርካቶች ናቸው። ህንዳዊያንን እና በካሪቢያን ደሴቶች ውስጥ የሚገኙ ህዝቦችን እንደ ምሳሌ መመልከቱ በቂ ማሳያ ነው። እንግሊዞች የዛሬዋን አሜሪካን ለመፍጠር ያደረሱት ግፍ እና መከራ እንዲህ ባለች ምጥን ፅሁፍ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ዛሬ ግን አሜሪካ ማለት ምን ማለት እንደሆነች ብነግራችሁ ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብኛል። ከእንግሊዝ መለስ ብለን ሌሎቹን የአውሮፓ ሀገሮች ብንመለከት ደግሞ አፍሪካን እንዴት አድርገው ተቀራምተው ቋንቋችንን፣ ባህላችንን፣ እምነታችንን በርዘው በሰባዊነት ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብ የሚዘገንን ግፍ ፈፅመውብናል። በባሪያ ንግድ እና በቅኝ ግዛት ሳቢያ ጥቁርነት የደካማነት፣ የተገዢነት፣ የለማኝነት፣ እና የስንኩልነት መገለጫ ሆኖ ቀርቷል። በሰው ልጆች ላይ የማይሽር ጠባሳ ጥለውብን አልፈዋል። ይህ የሆነው ግን ሀገራቸውን ለመገንባት፣ ለዛሬው ትውልዳቸው እኛ አፍሪካዊያን ባህር ዋኝተን፣ በረሀ አቋርጠን “ሀገሬ ላይ ሰው ከምሆን አውሮፓ ውስጥ ዛፍ ብሆን ይሻለኛል” እንድንል ያደረጉንን ሀገሮች ለማስረከብ ነው።

የኛው ምኒሊክም ታዲያ ግዛታቸውን ለማስፋፋት እና ለማስገበር በወቅቱ እራሳቸውን እንደ ግዛት ቆጥረው ያስተዳድሩ የነበሩ፣ የራሳቸው ቋንቋ፣ እምነት፣ ህግና ደንብ ያላቸው፣ የራሳቸው ሉአላዊ ድንበር የነበራቸውን ‘ሀገሮች’ ወረው በፈርጣማ ከፈፀሙት አሸንፈው አስገብረዋቸዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ ልክ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ492 ዓ.ዓ ፐርሺያዊያን ግሪክ ላይ ካደረጉት ወረራ ጀምሮ እስከ ቅርቡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር የ2018ቱ የዩናይትድ አረብ ኤመሬትስ የየመን ወረራ ድረስ እንደደረሱት ህልቆ መሳፍርት ግፎች የሚኒሊክ ጦር በተወራሪዎቹ ጦሮች እና ህዝቦች ላይ በአንድ ጦርነት ወቅት ለዛውም በአሁን ዘመን ዳኝነት እጅግ ‘ኋላ ቀር’ ሊባል በሚችል የጦር እና አስተዳደር ስርአት ውስጥ ሊደርስ የሚችለውን ግፍ እና በደል አድርሷል። ጠቃሚው እና ዋነኛው ነገር ግን ታሪኩን ለበቀል ወይስ ለእውቀት እና ከስህተቱ ለመማር? የሚለው ይመስለኛል። ይህንን እንደመነሻነት ካነሳሁ ዘንዳ ለዚህች ምጥን ወዳነሳሳኝ ርዕስ ልግባ። እስካሁን ወደ ርዕስህ አልገባህም ወይ? ገብቻለሁ አይዟችሁ።

ከላይ እንደጠቀስኩት እምዬ ምኒሊክ የአሁኗን ኢትዮጵያ ከመስራታቸው በፊት ትናንሽ ማህበረሰብ ሆነው በየግል አስተዳደራቸው በተበታተነ ሁኔታ የኖሩ ከነበሩት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል የሙርሲ ህዝብ አንዱ ነው። ሙርሲዎች እና በደቡብ ኦሞ አካባቢ የሚገኙት ጎረቤቶቻቸው በኢትዮጵያ አስተዳደር ውስጥ በይፋ የተካተቱት የአፄ ምኒሊክ ጦር የኬንያ እና ሱዳን ድንበር የሆነውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ቆላማ አካባቢዎች በወረረበት በ19ኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻ አመታት ላይ ነበር። የህ የኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ አካባቢ በብዙ ትናንሽ ቁጥር ያላቸው እና እንደየወቅቱ ከሚኖረው የአየር ሁኔታ ጋር እራሳቸውን እያስማሙ በተደጋጋሚ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ህይወታቸውን በመሰረቱ ህዝቦች የተያዘ ነበር። ነዋሪዎቹ ዘለግ ላለ ጊዜ ቦታው ላይ ረግተው የማይቀመጡ በመሆኑ ሀገርን ከልሎ ለማስቀመጥ አመቺ አልነበሩም። አሉ ሲባሉ የሉምና ድንበር ላይ ያሉ በመሆናቸው ባእድ ወራሪ ቢመጣ የወቅቱ መንግስት ድንበሩን በቋሚነት እንዲከላከል የሚያስችሉት አልነበሩም። ሙርሲዎች ዛሬም ድረስ እንደሚታወቁት ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ታሪካቸውን በዋነኛነት በሶስት የታላላቅ ፍልሰት ዘመኖች የፃፉ ህዝቦች ናቸው። የሙርሲን ያለፈውን ከ150 እስከ 200 አመት ድረስ ያሉትን ሶስት ታላላቅ የፍልሰት ታሪኮች ብንመለከት የህዝቡን የአኗኗር ዘይቤ እና ፖለቲካዊ ማንነት አገነባብ በቀላሉ ለመረዳት እንችላለን።

የመጀመሪያው ፍልሰት በመካከለኛው የ19ኛ ክፍለዘመን የተደረገ ሲሆን ከምዕራብ አቅጣጫ ተነስቶ የኦሞ ወንዝን በማቋረጥ ዛሬ ደቡብ ሙርሲ ወደሚባለው አካባቢ (ኩሩም) የሰፈረበት ነው። ይህ ፍልሰት በሙርሲ ፖለቲካዊ ማንነት ውስጥ ጉልህ ሚና እንደተጫወተ የሚታመንለት ታላቅ ጉዞ ነው። ቀጣዩ ፍልሰት በ1920 ዎቹ እና 30ዎቹ የተሻለ የውሀ አቅርቦት ወዳለው ወደ ሰሜን አቅጣጫ የተደረገ ነበር። በዚህም የዛሬውን የሙርሲ ሰሜናዊ ድንበር የሆነውን የማራ ወንዝን ለመያዝ ችለው ነበር። በ1987 የተደረገው ሶስተኛው የሙርሲ ፍልሰት ወደ ታችኛው ኦሞ ሜዳማ አካባቢዎች የተደረገው ሲሆን ከጎረቤታቸው የአሪ ህዝብ ጋር በተደጋጋሚ የድንበር እና ሀብት ውዝግብ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗቸዋል። በዚህኛው የፍልሰት ሂደት ግዛታቸው በግብርና ወደሚተዳደሩት የአሪ ህዝቦች እጅግ የተጠጋ በመሆኑ ለግንኙነቶቹ እና ግጭቶቹ እንደ መንስኤ ሊጠቀስ ችሏል። በኋላ ላይ በሌሎች ጎረቤቶቻቸው የቦዲ ህዝቦች የተያዘው የላይኛው ማጎ ሸለቆ አካባቢም ሌላው የሶስተኛው ፍልሰታቸው ማረፊያ ነበር።

ሙርሲዎች እያንዳንዱን ፍልሰት እንደ ህዝብ ከመጀመራቸው በፊት ጥቂት ቤተሰቦችን አስቀድመው ይልካሉ። እነዚህ ቀዳሚ ቤተሰቦች የቦታውን ለምነት፣ አመቺነት እና ከጠላት የፀዳ መሆን ካረጋገጡ በኋላ ሌሎች የብሄረሰቡ አባላት በቡድን እና በተናጠል በመሆን ይከተሏቸዋል። ሙርሲዎች ስለ ፍልሰቶቻቸው ሲናገሩ “የሁሉም ፍልሰቶች ምክንያት የተፈጥሮ መቀያየር ነው” ይላሉ። ሙርሲዎች አርብቶ አደሮች እንደመሆናቸው ለከብቶቻቸው የተመቸ ግጦሽ እና ውሀ፣ ለሚያበቅሉት አዝዕርት ለም መሬት እና ተስማሚ የአየር ጠባይ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ፤ በጀግና ተዋጊዎቻቸው የሰፈሩባቸውን አካባቢዎች ይጠብቃሉ። በመግቢያዬ ላይ ስለኢትዮጵያ የታሪክ አሰናነድ እንዳመለከትኩት ይህ የፍልሰት ታሪክ በሙርሲ ጎረቤቶች አሊያም በወራሪ የምኒሊክ ወታደሮች ቢተረክ በዘላንነት የሚኖሩ ሰዎች በስነስርአት እንዲኖሩ እና ከትልቁ የምጣኔ ሀብት ክፍፍል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም የተሻለ የደህንነት ከለላ እንዲኖራቸው የተደረገ የማስተዳደር ስርአት ወይ ደግሞ የተረጋጋ ህይወታቸውን ሊበጠብጡ እንደመጡ የጠላት ሀይሎች ተደርጎ መነገሩ የማይቀር ነው። እውነታው ግን የትኛውም የአለማችን ህዝብ ታሪክ በፍልሰት እና ግዛትን ለማስፋፋት በሚደረጉ የትግል ታሪኮች ‘ያሸበረቀ’ መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው። ሁሉም ህዝብ ለልጅ ልጆቹ የተሻለ የኑሮ ደረጃን ለማዘጋጀት እንዲሁም በራሱ ላይ የመጡ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ከቦታ ቦታ ሊዘዋወር፣ በጎረቤቱ ላይ ሊነሳ፣ በወዳጁ ላይ ጦሩን ሊሰብቅ ይችላል።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ የተገነባቸው የተለያዩ ራስ ገዝ አስተዳደሮችን በአንድ ጥላ ስር በማሰባሰብ በተፈጠረ ስርዓት ነው። የአፄ ሚኒልክም ‘ንጉሰ ነገስት’ የሚለው ማዕረግ ምንጭ ይኸው የአስተዳደር ስርአት ነው። ሁሉም አካባቢ የራሱ ንጉስ አለው (የጅማ ንጉስ፣ የወላይታ ንጉስ፣ የጉራጌ ንጉስ፣ የሸዋ ንጉስ፣ የወሎ ንጉስ፣ የትግሬ ንጉስ፣ የሀረር ንጉስ፣ የከፋ ንጉስ ...) የሁሉም ነገስታት ንጉስ ደግሞ አፄ ምኒሊክ ሆኖ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ተመሰረተች። ይህች ሀገር ታዲያ አንዱ ክፍሏ ቢቀነስ ልክ እንደ ‘ጂግሶው’ ጨዋታ የጎደለች ሀገር እንጂ ሙሉዋ ኢትዮጵያ አትገኝም። ምናልባትም ‘ኢትዮጵያ’ ብለን መጥራት የማንችለው እና ምናልባትም ሌላ የግዛቶች ስብስብስ ስያሜ የሚያስፈልገው የብትን ህዝቦች መኖሪያ አካባቢ ትሆን ይሆናል። የሙርሲ ህዝብም ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ካደረጉ ህዝቦች መካከል የሚጠቀስ፣ የዳር ድንበሯ ዘብ፣ የህብረ ብሄራዊነቷ ማሳያ፣ የሀገር በቀል እውቀቶቿ መገለጫ፣ የአፍሪካዊነቷ አሻራ፣ የአንድነቷ ማሰሪያ ሆነ የኖረ የሚኖር ህዝብ ነው። ቸር ይግጠመን


26 views0 comments

コメント


bottom of page