ውበት እንደየማህበረሰቡ፣ ዝቅ ሲል ደግሞ እንደየ ግለሰቡ ይደፈየናል። ለእያንዳንዱ የውበት ዘርፍ የሚሰጠው ትንታኔም በብዛት የግል ልምድን እና ምልከታን ማዕከል ያደረገ ነው። በዚህች ምጥን ፅሁፍ የሰውነት ላይ ውበት መጠበቂያዎችን ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 82 ብሄሮች መካከል በሀገራችን ደቡባዊ ክፍል በኦሞ ሸለቆ ውስጥ በሚገኘው ‘ሙርሲ’ ማሳያነት አጫውታችኋለሁ።
ከተሜ እራሱን ለማስዋብ ከብረት የተቀጠቀጡ፣ ከተለያዩ የከበሩ ማዕድኖች የተበጁ ጌጣጌጦችን የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ላይ በተለይ ደግሞ በጆሮው እና በጣቶቹ ላይ በማንጠልጠል ይዋባል። የከተሜ ውበት አንዱ መገለጫ የማዕድኑ ውድነት እና የቀለጠው ብረት ንድፍ ማማር ነው። የከተማ ሴቶች የተለያዩ ይዘት ያላቸው ቀለሞችን ከናፍሮቻቸው እና የአይን ቆባቸው ላይ በመቀባት ሰውነታቸውን ያስውባሉ። የእጅ አንባር፣ የጣት ቀለበት፣ የአንገት ሀብል እና የጆሮ ጌጦችን በመሸመት በተለያዩ ቀለማት እና ዲዛይኖች አጊጠው ለራሳቸው የመንፈስ መታደስን፣ ለተመልካች ደግሞ ውብ እይታን ይፈጥራሉ። በአሁኑ ግዜ ደግሞ በተለይ በምዕራቡ አለም በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለው የቆዳ ላይ ንቅሳት ሌላው የውበት መገለጫ ሆኗል። በርግጥ ንቅሳት በኢትዮጵያ ቀደምት የውበት መሳሪያ እንደነበር በተለይ የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ታሪክ ያስረዳናል። የሰሜን ሴቶች ድዳቸውን በመነቀስ(በመወቀር) አይበሉባቸውን እና አንገታቸውን በተለያየ የንቅሳት ንድፍ በማስዋብ በውበታቸው ግነት ሲወዳደሩ፣ ወንዶችን ሲያማልሉ፣ ሲያሽኮረምሙ ኖረዋል። ይህ የንቅሳት መንገድ ታዲያ በባህላዊ መንገድ ቆዳን ወይም ድድን በመርፌ አሊያም በሹል ብረት በመብጣት የሚከናወን በመሆኑ እጅግ ከፍተኛ ህመምን የሚያስከትል ነው። ሆኖም የንቅሳት ውበት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ፣ የአካባቢው ማህበረሰብም የውበት መለኪያ እንደሆነ አምኖበት ለዘመናት ኖሯል።
በጠቅላላው በሰውነት ላይ የሚደረጉ እና የሚቀቡ ነገሮች የዘወትር ገፅታችንን ለ’ኛ ወይም ለተመልካች ማህበረሰባችን ‘ውበት’ የሚለውን መስፈርት በሚያሟላ መልኩ ሲቀይሩት እና የውስጥ ደስታ መፍጠር ሲችሉ በውድ ዋጋ እየተገዙ አገልግሎት ላይ ይውላሉ። እነዚህ ሰውነት ላይ የሚደረጉ እና የሚቀቡ ነገሮች በሙርሲዎች ዘንድ ከውበት ያለፈ ግልጋሎት አላቸው። ከአገልግሎታቸውም ባለፈ እንደዘመነኛ ጌጦች ለጆሮ የሚከብድ ዋጋ ሲጠራባቸው አይሰማም።
ሙርሲዎች እራሳቸውን ለማስዋብ የከንፈር ላይ ሸክላ (በከንፈር ላይ ሸክላ ዙሪያ ተጨማሪ ለማንበብ https://www.southomotheatre.com/post/%E1%8B%8D%E1%89%A0%E1%89%B5-%E1%88%B2%E1%88%88%E1%8A%AB ይጎብኙ)፣ የጆሮ ጉትቻ፣ የሰውነት ቀለም፣ ንቅሳት፣ አምባር፣ አልቦ እና የአንገት ጌጥ ያደርጋሉ። የደገኞች ምላጭ በአካባቢው ከተዋወቀ በኋላም ፀጉራቸውን በተለያየ ቅርፅ በመላጨት የውበት መለኪያቸውን አሳድገዋል። ሙርሲዎች በፆታ ሳይገደቡ ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ እኩል የመዋቢያ ጌጦችን በመጠቀም ሲዋቡ እንመለከታለን። ለምሳሌ የጆሮ ጉትቻን ብንወስድ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በወንዶች ዘንድ እንደ መዋቢያ የማያገለግል ሲሆን በሙርሲዎች ግን ያለምንም ችግር ይደረጋል። ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ ጆሮዎቻቸውን በምላጭ ወይም በስለት በመሰንጠቅ ሰፊ ቀዳዳ እንዲፈጥር ካደረጉት በኋላ ቁስሉ ሲደርቅ የተለያየ መጠን ያላቸውን ሸክላዎች በማስገባት ይዋባሉ።
አምባር እና አልቦም እንዲሁ በሁሉም የሙርሲ ወንዶች እና ሴቶች የሚደረግ መሰረታዊ የመዋቢያ ግብዓት ነው። የሙርሲ ሴቶችን አምባር ለየት የሚያደርገው ነገር ግን ከውበት መጠበቂያነት በዘለለ የሚሰጠው ግልጋሎት ነው። የሙርሲ ሴቶች አምባርን እንደ ደህንነት መጠበቂያ ይጠቀሙበታል። ጥፊ የልብ ስለማያደርስ፣ ቡጭሪያም ከአንጀት ጠብ ስለማይል፣ ቡጢም የወንዶች ነውና የገጠማቸውን ባላንጣ፣ በመንገዳቸው የገባባቸውን ደንቃራ ከነሀስ/መዳብ በተሰራው ከግማሽ በላይ ክንዳቸውን በሚሞላው አንባራቸው ‘እንካ ቅመስ’ በማለት እራሳቸውን ይከላከላሉ፤ የሚሰነዘርባቸውንም ዱላ ይመክታሉ። በዚህ ‘ኡላ’ በተባለው የእጅ አንባር የመማታት ጥበብ ዝም ብሎ የሚሞከር አይደለም። ወጣት የሙርሲ ሴቶች ልምድ ባላቸው ታላላቆቻቸው እየታ ስር በመሆን ጥንድ ጥንድ ሆነው ዘለግ ላለ ጊዜ ይለማመዳሉ። በሚገባ መመከት እና ኢላማቸውን መምታት ሲችሉ በልበ ሙሉነት ይንቀሳቀሳሉ።
ንቅሳት ለሙርሲ ወንዶች እና ሴቶች እንደ ከተሜዎች በዘመነኛ ማሽን ወይም እንደ ሰሜን ኢትዮጵያዊያን በቀጭን መርፌ ተጠቅጥቆ ቀለም የሚቀባ፣ በኋላም የፈሰሰው ደም ሲደርቅ የተቀባውን አረንጓዴ ቀለም ይዞ የሚቀር የቀናት ብቻ ህመም የሚስተናገድበት ሂደት አይደለም። የሙርሲ ሴቶች ልክ አጎጠጎጤያቸው ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምር እና ጡታቸው ቅርፅ መያዙ ሲረጋገጥ የጡታቸውን ቅርፅ ተከትሎ በክብ ቅርፅ ቆዳቸው በትንሽ በትንሹ ይቆረጣል። የተቆረጠው የቆዳቸው ክፍል ሲደርቅ ታዲያ ጠባሳው ተመሳሳይ ንድፍ ያለው ውበት ይፈጥራል። ክንዳቸው፣ ጀርባቸው፣ ደረታቸው እና ሆዳቸው ላይ የሚያደርጉት ንቅሳትም በተመሳሳይ ቆዳቸውን ቆርጦ በማውጣት እና ቁስሉ ጠባሳ እንዲጥል በማድረግ የሚፈጠር እጅግ ከፍተኛ የሆነ ህመም ያለው የመዋቢያ ስልት ነው።
የሙርሲ ወንዶች እና ሴቶች የሚዋቡበት ሌላው የውበት ግብዓት የገላ ላይ ቀለም ነው። ሙርሲዎች እንደከተሜዎች ከናፍሮቻቸውን ብቻ ለይቶ በመቀባት የተሟላ ውበት ማግኘት አይችሉም። በተለያዩ የቱሪዝም ፎቶዎች እና ምናልባትም ጥቂት ዘጋቢ ፊልሞች ላይ እንዳያችሁት ሙሉ ሰውነታቸውን በተለያየ የጭቃ ቀለም፣ በተለያየ ንድፍ ተቀብተው ያሸበርቃሉ። በአሁኑ ግዜ ይህ የቀዳ ላይ ቀለም ለበርካታ ሙርሲዎች ከባህልነት ባለፈ የማይነጥፍ የገቢ ምንጭ ሆኖላቸዋል። ለዚህም ይመስላል አንዳንድ ግዜ ከባህሉ በጥቂቱም ቢሆን ባፈነገጠ መልኩ ሲዘወተር የሚስተዋለው። በመሰረቱ የሙርሲ ወጣቶች በተለይ ወንዶቹ ለአቅመ አዳም ሳይደርሱ በተለያየ ንድፍ ያሸበረቀውን የቆዳ ላይ ቀለም አይቀቡም። ምክንያቱም ጭቃውን ቀምመው የሚቀቡበት ዋነኛው ምክንያት ከእድሜ አቻዎቻቸው የተሻለ ውብ መሆናቸውን ለማሳየት እና ሴቶችን ለማሽኮርመም ነው። ስለዚህ ይህ የመዋቢያ ስልት ህፃናትን እና ያገቡ ወንዶችን አይመለከትም ማለት ነው። ነገር ግን ከላይ እንደተጠቀሰው የገቢ ምንጭነቱ እና ጎብኚዎችን የበለጠ የሚስብ በመሆኑ ሁሉም ሲያደርጉት ይታያል። ትክክለኛውን የሙርሲዎች ህይወት ያየን እንደሆነ ግን የቆዳ ላይ ቀለም ከስነውበትነቱ በበለጠ በጤና መጠበቂያነቱ ሲዘወተር እናያለን።
የሙርሲ ህፃናት በማሀበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን እና የህልውናቸው መሰረት የሆኑትን ከብቶቻቸውን የመጠበቅ፣ የመመገብ እና በሰላም ወደ ቤታቸው የመመለስ ከፍተኛ ሀላፊነት አለባቸው። የሙርሲ ከብቶች በማንኛውም ሁኔታ ጠባቂ አጥተው ለረሀብ ወይ ደግሞ ለጠላት መጋለጥ የለባቸውም። ስለዚህ ጠባቂዎቻቸው ዘወትር በመልካም ጤንነት እና በንቁ መንፈስ የተዘጋጁ መሆን አለብቻው። ለዚህም ታዲያ የአካባቢውን ሀሩር መከላከል የሚችለው ተፈጥሮ ያደለቻቸውን በአይነቱ ለየት ብሎ ለሰውነት ቆዳ ተስማሚ የሆነውን እርጥብ ጭቃ (ዘመነኞች ወደ ወንዝ ዳርቻ ወይም ፀሀያማ አካባቢውች ሲሄዱ ቆዳቸውን ለመጠበቅ እንደሚቀቡት የፀሀይ መከላከያ ቅባት (ሰን ስክሪን)) በመቀባት እራሳቸውን ከፀሀይ ንዳድ ይከላከላሉ። ጭቃው ፀሀይን ከመከለሉም ባሻገር እረኞቹ በቁጥቋጦዎች ዙሪያ ሲሯሯጡ ሰንበሌጥ መሰል ሳሮች እንዳይቆርጧቸው ይከላከላል። በሙርሲ አካባቢ ያሉ ተፈርፋሪ ድንጋዮች እና የአፈር አይነቶች መድሀኒታዊ ጠባይ ያላቸው በመሆኑ ማህበረሰቡ በሽታን ለመከላከል ወይም ለመፈወስ ይጠቀምባቸዋል። የማያልቅበት ፈጣሪ ሲሰጥ አይሰስትምና እነዚህ የተፈጥሮ ትሩፋቶች ለሰውነታቸው ተስማሚ ከመሆናቸውም በላይ የተለያየ ቀለም ያላቸው ናቸውና በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ጤናቸውን እየጠበቁ በቀለማቱ እና በንድፍ ጥበባቸው ደግሞ ይዋባሉ። ታዲያ “ሲያጌጡ ይመላለጡ” አባባል ለሙርሲ ይሰራ ይሆን?
Comentários