top of page
Search
  • mastu89

ቅብብሎሽ

Updated: Nov 22, 2021

የዛሬው ምጥን ፅሁፌን የምጀምረው በሁለት ተያያዥ ጥያቄዎች ነው። 1. ሀብት ለእርስዎ ምንድን ነው? 2. ሀብትዎን ለመጠበቅ ምን ያደርጋሉ? ምላሽዎን ከራስዎ አሊያም በአካባቢዎ ካለ ሰው ጋር ወይ ደግሞ ከዚህ ፅሁፍ ስር በአስተያየት ማስቀመጫው በማስፈር ሊወያዩበት ይችላሉ። የብዙዎቻችን መልስ ግን ሀብት ማለት ገንዘብ፣ እውቀት (የአሁኑን ዘመን እንጃ እንጂ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበርንበት በ90ዎቹ ከገንዘብ እና ከእውቀት ማን ይበልጣል የሚል የጦፈ ክርክር የየትምህርት ቤቶቹ የአርብ ከሰአት ክንውን ነበር) ውበት፣ ንብረት ወዘተ ሊሆን ይችላል። አለማችን ከጥግ እስከ ጥግ በካፒታሊዝም ፅንሰ ሀሳብ ተወጥራ ህዝቦቿ ግላዊ ሀብት ለማካበት ያለ እረፍት ሲታትሩ፣ ወንጀል ውስጥ ሲዘፈቁ፣ ሰባዊነትን ሲፈታተኑ እናስተውላለን። በደፈናው ስናየው ግን ብዙዎቻችንን የሚያስማማው የሀብት አይነት ገንዘብ ሲሆን የጥበቃ መንገዳችን ደግሞ ባንክ ቤት ወይም ግላዊ ጠባቂዎች ናቸው። ዳሩ ግን ይህ እውነታ በተለይ በከተማዎች ውስጥ ለምንኖር ይሁን እንጂ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መገለጫ አይደለም። ዛሬ በዚህች ምጥን ገንዘብ አልባ ስለሆነ ማህበረሰብ አወጋችኋለሁ። ይህ ማህበረሰብ ለወረቀት ገንዘብ ቁብ የማይሰጥ፣ የአለም ሀብት ትርጉም የማይሰጠው፣ የውጭ ምንዛሪ መጨመር እና የገንዘባችን ዋጋ ማጣት የማያሳስበው በራሱ አለም ውስጥ የሚኖር ልዩ ማህበረሰብ ነው። ሙርሲ!

ሙርሲዎች ሀብታቸውን የሚመዝኑት በወረቀት ወይ ደግሞ ከባንክ ቤት በሚሰጥ አንዲት ብጣሽ ደብተር ላይ በተፃፈ የቁጥር ድርድር አይደለም። ይልቁንስ በአይኑ በሚያየው፣ በእጁ በሚዳስሰው የከብቱ ብዛት፣ ባለው የመሬት ስፋት እና የምርት አይነት ነው። ከብት ማለት ለሙርሲ ህይወት ማለት ነው። ከብት ማለት ለሙርሲ ቀለብ ማለት ነው። ከብት ማለት ለሙርሲ ቤተሰብ ማለት ነው። ሙርሲዎች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች ጥቂት የጓሮ አትክልቶችን ወይም እንደማሽላ ያሉ ለአካባቢው አየር የሚስማሙ አዝዕርቶችን በመዝራት ቀለባቸውን ይሰፍራሉ። ይህ የሚሆነው ታዲያ በከብቶቻቸው ጫንቃ፣ በላሞቻቸው እዳሪ ነው። የሙርሲ ወጣቶች የእለት ተእለት ቀለብ ትኩስ የከብት ደም በወተት ነው። በአካል እና በመንፈስ እንዲጠነክሩ፣ እንዲጀግኑ በየቀኑ ደም መጠጣት አለባቸው። በየቀኑ ትኩስ ደም ለመጠጣት በየቀኑ ከብት ሊያርዱ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ነገሩ የሚከወነው እንዲህ ነው፡ ከብቶቹ ጠዋት ወደ ግጦሽ ሲወጡ ከአንገታቸው ወረድ ብሎ የሚገኘውን የደምስር በመብጣት ትኩስ ደም ይቀዳሉ። የሚፈልጉትን ያህል ደም ካገኙ በኋላ የተበጣው ቦታ ደም ማፍሰስ እንዲያቆም በሀገር በቀል እውቀታቸው ካዳበሯቸው የቅጠል መድሀኒቶች መካከል ደም የሚያቆመውን ይቀቡታል። አለቀ፣ እነሱም ትኩስ ደማቸውን ይዘው የሚቀላቅሉትን ወተት ለማለብ ወደ ላሚቷ፣ ከብቱም ምንም እንዳልተፈጠረ ያህል ወደ ግጦሹ። የሙርሲ ወጣት ለአቅመ አዳም ደርሻለሁ፣ ቤተሰብ መመስረት ዘሬን ማስቀጠል እፈልጋለሁ ያለ እንደሆነ ቢያንስ 38 ከብቶች በጥሎሽ ለሙሽሪት ቤተሰብ መስጠት አለበት። ይህንን የከብት ብዛት ማቅረብ ካልቻለ ቆሞ ቀር፣ ደካማ እንዲሁም ዘሩን ማስቀጠል ያልቻለ ድኩማን ተደርጎ ይቆጠራል፣ ይዋረዳል። ሙርሲ በልጆቹ መሀል አሊያም ከጎረቤቶቹ ጋር አለመስማማት ቢገጥመው እጅግ ውድ የሆነ ሀብቱን ‘ከብትን’ በማረድ ስለሰላም ይመክራል፣ ኑሮውን ለማቅናት አመቺ የግጦሽ ቦታ እና የውሀ ምንጭ ፍለጋ ሲዘዋወር ጎኑን ማሳረፊያ ትናንሽ ከሳር እና ልምጭ በሚሰሩ ጊዜያዊ ጎጆዎቹ ውስጥ አረፍ ለማለት ቢያሻ በከብት ቆዳ በተመቻቸው መደቡ ነው፣ የሙርሲ ሴቶች ለዘመናት ገላቸውን የሚሸፍኑት ከከብት ቆዳ በተሰራ ልብስ ነው፣ ሙርሲ የሚያከብረው ጥቁር እንግዳ ቢመጣበት ፍቅሩን ለመግለፅ ከብቱን ይሰዋል። ታዲያ ሙርሲ ካለከብት ህይወት የለውም ብንል ማጋነን ይሆንብን ይሆን?

ይህ የህይወቱ መሰረት የሆነውን ከብት ደህንነት ታዲያ በምን መልኩ ይጠብቃል? እንዴትስ ባለ የተደራጀ አሰራር ከብቶቹን ከስጋት ነፃ አድርጎ ማሳደር ይችላል? ከተሜ የወረቀት ሀብቱን በባንክ ያስቀምጣል፤ ባንክ ማስቀመጥ ያልፈለገውን/ የማይችለውን ደግሞ ጠባቂ በመቅጠር ያስጠብቃል። ሙርሲስ? የከብት ባንክ መቼም አልተጀመረም፣ የህይወት መሰረቱ የሆኑትን ከብቶቹን የሚጠብቁ በስፖርት ሰውነታቸውን ያዳበሩ ጎረምሶችን አምጥቶ አይቀጥር ነገር እኛን የሚያማልለን ገንዘብ የለውም። ታዲያ በምን ይጠብቅ? መልሱ ቀላል ነው - በጠብመንጃ! ጠብመንጃ ለሙርሲ ከከብቶቹ ቀጥሎ አለኝ የሚለው ውድ ንብረቱ ነው። ማንኛውም የሙርሲ ህፃን በግምት አስር አመት ከሞላው ጀምሮ አተኳኮስ ይለማመዳል፣ የራሱ ክላሺንኮቭ በስጦታ ይበረከትለታል። ከከብት ሀብቱ በተጨማሪ ጀግንነቱ የሚለካው በአልሞ ተኳሽነቱ፣ በአልነካም ባይነቱ ነው። ጠብመንጃ በቁጥር ከአስር ሺህ እምብዛም ፈቅ ለማይሉት የሙርሲ ህዝቦች የህልውናቸው ማስጠበቂያም ጭምር ነው። መሬታቸውን የሚጠብቁበት፣ ንብረቶቻቸውን ከጠላት የሚሸሽጉበት ዋስትናቸው ነው። በአካባቢው ተጎራባች ህዝቦች እንዲሁም በአንዳድ የመሀል ሀገር ሰዎች ላይ በሚደርሱ አደጋዎች ሳቢያ የኢትዮጵያ መንግስት የሙርሲዎችን ጠብመንጃ ለማስፈታት ጥረት አድርጎ የነበረ ቢሆንም መቶ በመቶ ስኬታማ አልሆነም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በአንድ ወገን የሀገር ድንበር ጠባቂ በመሆናቸው፣ በሌላ ደግሞ ጠብመንጃን እንደ አካላቸው የሚያዩ በመሆናቸውና ከመንግስት እይታ ከልለው በማኖራቸው የመንግስት ጣልቃ ገብነት ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል። በርግጥ መንግስት የእውነት ጠብመንጃቸውን ማስፈታት ይፈልጋል ወይ? የሚለው ጥያቄ ብዙ ትንታኔ የሚሻ ነው። አንዲት ምሳሌ አየት አድርገን ሌላውን በሌላ ፅሁፍ እንመለስበታለን። ኢትዮጵያ በመሬት የተከበበች ሀገር እንደመሆኗ በአራቱም ማዕዘን በሌሎች ህዝቦች የተከበበች እና ደህንነቷ ሁል ግዜ ስጋት ውስጥ ያለ ሀገር ነች። ታዲያ መንግስትም የህዝቡን ደህንነት እና የሀገሩን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ወጥቶአደሮችን በየድንበሩ ማሰለፍ ይጠበቅበታል። በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ደረጃ እና ዘወትር ከማይለያት የውስጥ እና የውጭ ትንኮሳ አንፃር ወጥቶአደሮችን በቋሚነት ማሰለፍ ትችል ይሆን? መልሱ ግልፅ ይመስለኛል። ሙርሲዎችም ፈልገውት ባይሆንም በደቡብ ምዕራብ በኩል ያለውን የሀገሪቱን ድንበር ቀጥ አድርገው እየጠበቁ በመሆኑ መንግስት ጠብመንጃቸውን ጨርሶ ላለማስፈታት በቂ ምክንያት የሚያገኝ ይመስለኛል። የሆነ ሆኖ በአሁኑ ግዜ ብዙዎቹ የሙርሲ ጠብመንጃዎች በመንግስት በህጋዊነት የተመዘገቡ በመሆናቸው የህገወጥነት ስጋቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀርፏል ማለት ይቻላል።

ጠብመንጃ በአጠቃላይ ለሙርሲ ከብቶቻቸውን፣ ውሀቸውን እና መሬታቸውን ከማስጠበቂያነት ባሻገር የብሄረሰቡ የድህንነት ዋስትና፣ የእያንዳንዱ ወጣት የኩራት መገለጫ ነው። ጠላትን አልሞ መግደል የውንድነት ጥግ የኩራት ምንጭ ነው። ለዚህም ማሳያ እንዲሆን ሙርሲዎች ክንዳቸው ላይ የገደሉትን ጠላት ቁጥር ተነቅሰው ያኖሩታል። ንቅሳታቸው በታየ ቁጥር የሚቀርባቸው ይርበደበዳል፣ ነገር ሊፈልጋቸው የሚሻ ቢኖር ከግብታዊነት ይቆጠባል።

ዛሬ ዛሬ ግን ሙርሲ በቱሪስቶች ብዛት እና በመንግስት ከፍተኛ ጫና ከልማዶቻቸው ውጪ ለሆኑ ነገሮች ተገዢ እየሆነ መጥቷል። በፊት ትርጉም የማይሰጠው የወረቀት ገንዘብ ዛሬ የደስታው ምንጭ፣ የእለት ተእለት ኑሮው መሰረት እየሆነ ነው። ‘ዘመናዊነት’ በሚል በሽታ የተለከፉ አንዳንድ ግለሰቦች በሚያደርሱት ጫና የማንነቱ መገለጫዎች የሆኑ ድርጊቶቹን እየተወ ለምዕራባዊያን ባህል ተገዢ ለመሆን እየተንደረደረ ነው። ተተኪው ትውልድ ከቆዳ የሚሰራ ልብሳቸውን ረስቶ በሳምንት ውስጥ ተቦጫጭቆ ወደሚሰራው ጨርቅ እያደላ ነው። ‘መሻሻሉ’ እና ወደ ብዙሀኑ የአኗኗር ስልት መግባቱ ሙሉ በሙሉ ክፋት ባይኖረውም የማንነት አሻራውን ጥሎ አዲስ ማንነት መያዙ ግን የማህበረሰቡን ቀለም የሚያደበዝዝ ብሎም የሚያጠፋ ተግባር ነው። ይህ ወረርሺኝ ያሳሰበው የአካባቢው ተወላጅ ኦሊሰራሊ አሊቡዪ እየመጣባቸው ያለውን ማዕበል እንዴት ወደ በጎ ነገር እንደሚቀይረው አሰላሰለ። በእንድ ወቅት ለጉብኝት ከመጡ የአውስትራሊያ ዜጎች ጋር በመቀራረብ የውጪ እድል እንዲያመቻቹለት አድርጎ ወደ አውስትራሊያ አቀና። ኦሊ ለሁለት አመታት እንግሊዘኛ ቋንቋን ተምሮ የሙርሲ የማንነት ዘብ ለመሆን በቂ እውቀት እና ቁርጠኝነት ይዞ ተመለሰ። ከብሄረሰቡ የመጀመሪያው ከሀገር የወጣ ጉብል እንዲሁም ቢያንስ ሶስት ቋንቋ በመናገር ከቱሪስት አስጎብኚዎች፣ ከቱሪስቶች እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቀላሉ መግባባት የሚችል በመሆኑ የሚመጡ እንግዶች ሁሉ በቀጥታ የሚያገኙት እሱን ሆነ። በዚህ ጊዜ ታዲያ የሙርሲ ገፅታ ግንባታ እና የባህል አለመበረዝ ሙሉ ሀላፊነት እሱ ላይ ወደቀ።

ኦሊ በተደጋጋሚ ከሚያገኛቸው ጋዜጠኞች እና የፊልም ባለሞያዎችም የመቅረፀ ምስልን ምንነት እና ጥቅም ተረዳ። በዚህ ግዜ ነበር ኦሊ በዚህ ልዩ መሳሪያ የህዝቡን ማንነት ለትውልድ ለማቆየት እንዲሁም ትክክለኛ ቀለማቸውን ለማሳየት ሊጠቀምበት እንደሚገባ የተረዳው። በዚህም ከተደጋጋሚ ጥረት በኋላ ከእንግሊዛዊው የፊልም ባለሞያ ቤን ያንግ ጋር በመተባበር የመጀመሪያውን ፊልም ‘ቀረፃ ከሙርሲ ጋር’ (http://www.shootingwithmursi.com/) ሰርቶ በአለም አቀፍ መድረኮች ለእይታ አበቃ። የሚገርመው ነገር ግን ይህ ፊልም በኢትዮጵያ ውስጥ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ (https://www.facebook.com/wku.edu.et) ውጪ አንድም ቦታ ታይቶ አለመታወቁ ነው። ኦሊ ለማህበረሰቡን ህልውናና እና እድገት ማነቆ የሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠላቶቻቸውን ማባረሪያ ከጠብመንጃ የተሻለ መሳሪያ ማግኘቱን ለአለም መሰከረ። ጠብና እና ጥላቻን በፍቅር እና ጥበብ በመቀየር ስለሰላም ለመስበክ ታጥቆ ተነሳ። ኦሊ ስለ ጠብመንጃ እና መቅረፀ ምስል ልዩነት ሲናገር እንዲህ ይላል፡ “የክላሺንኮቭ ጥይት በተወሰነ ርቀት እንድ ሰው ብቻ ሊገድል፣ አንድ ጠላት ሊያስቆም ይችላል የካሜራ ጥይት ግን በመላው አለም በመሰራጨት የማንም ነፍስ ሳይጠፋ በፍቅር እና በመረጃ በአንድ ጊዜ ሁሉንም መድረስ ይችላል” ይህ ሀሳቡ ፍሬ አፍርቶ ፊልሙ በአለም መድረኮች ለስምንት የታላላቅ ፊልም ፌስቲቫሎች የታጨ ሲሆን ሶስቱን አሸንፏል። ይህ ሽልማት እና አለምአቀፍ እውቅና ለኦሊ ምንም ነው። ይልቁንስ ኦሊን የሚያሳስበው ከመጪው ትውልድ ጋር የሚኖረው ቅብብሎሽ ነው። ኦሊ ለልጁ የሚያቀብለው ከአባቱ የተቀበለውን ጠብመንጃ ወይስ በጥረቱ ያገኘውን ካሜራ? እኛስ? ለልጆቻችን፣ ለተተኪዎቻችን የምናቀብለው ምንድን ነው?


210 views0 comments
bottom of page