top of page
Search
mastu89

ሀገር አፍቃሪው ማቴዎስ በቀለ

ከደብረ ኤሊያሱ ሸቅርቅር የቅኔ፣ ድጓ እና ምስጢር ሊቅ ቀኝጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ አይነ ግቡ ተማሪዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠራው ኢትዮጵያዊው ሁለገብ ከያኒ ማቴዎስ በቀለን ላስተዋውቃችሁ። በዚህች ምጥን ፅሁፍ የቴአትር ጥበብ ህይወቱን ብቻ በወፍ በረር ስለምንቃኝ ‘ሁለገብ ከያኒ’ እንበለው እንጂ በሌላ ህይወቱ ነፍሱን ለሀገሩ ያስገዛ ሰው ነበር። እንደ አባቶቹ ሁሉ በአጥንቱ ፍላጭ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር በብዙዎች ዘንድ እንደ ሞት መንገድ የሚቆጠረውን የውትድርና ሙያ፤ መቶ አለቃ ማቴዎስ በሙሉ ፍላጎቱ ለሁለት አመታት በሆለታ ገነት ወታደራዊ ሳይንስን ተምሮ እራሱን ለመሰዋዕትነት ያዘጋጀ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ነበር። ቀደም ሲል እንዳልኩት በዚህች ምጥን የማቴዎስ የቴአትር ጥበብ ህይወት ላይ ትኩረት ስለምናደርግ በወታደራዊ ማዕረጉ አንጠራውም፣ የውትድርና ህይወቱንም አናነሳም። ምናልባት በሌላ ፅሁፍ ወይም መረጃውን ማጠናቀር በሚችል አንባቢ ሊቀርብልን ይችላል።

ማቴዎስ ከዚህ አንዴ ከተጣባ እስከ ህይወት ፍፃሜ ድረስ የማይለቅ አዚዝ ባለው ‘የቴአትር ጥበብ’ በተባለ ልክፍት የተለከፈው ገና በትምህርት ቤት ሳለ በቅኔና ሚስጥር ጥበቡን የሚራቀቁበትን የልበ ብርሀኑ መምህሩን ቀኝጌታ ዮፍታሄ ንጉሴን እግር መከተል በጀመረ ግዜ ነበር። (በኢትዮጵያ የትምህርት ቤት ድራማ ታሪክ ውስጥ ከአርመናዊያንኑ እና ግብፃዊያኑ መምህራን ቀጥሎ ቴአትርን በመተርጎም፣ በማዘጋጀት እና በማስተዋወቅ ባለቅኔው ቀኝጌታ ዮፍታሄ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው (የኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ድራማን በሌላ ፅሁፍ እንመለስበታለን))። ቀኝጌታ ዮፍታሄ በጥልቅ አይናቸው መርምረው እውነተኛ ተሰጣኦ ያላቸውን ተማሪዎች ለዚህ ታላቅ የጥበብ ዘርፍ ያጩ ነበር። በሁሉም ጎኑ የተሳለው የያኔው አፍላ ማቴዎስም የመምህሩ አይን ማረፊያ ነበር። በዚህም ማቴዎስ በተለያዩ የትምህርት ቤት ድራማዎች ውስጥ በግንባር ቀደም ተዋናይነት ይሳተፍ ነበር። ከትምህርት ቤት በኋላም በወቅቱ በነበሩ ጋዜጦች ላይ ቋሚ አምድ በመያዝ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ይፅፍ የነበረ በመሆኑ ከልጅነቱ ጀምሮ ይዞት ያደገውን የጥበብ መንገድ የበለጠ ማስመሪያ፣ አእምሮውንና እጁንም የበለጠ ማፍታቻ መንገድ ማግኘቱን የአዲስ አበባ መካነ አዕምሮ የቴአትር ጥበብ መምህሩ ፋንታሁን እንግዳ በታሪካዊ መዝገበ ሰባቸው አስፍረውታል።

ማቴዎስ በቀለ በ1939 ዓ.ም በሙሉ አቅሙ ወደ ቴአትር ስራ ሲገባ እጁን ያሟሸው “የውሸት ተራራ”፣ “የሎግነሽ ጠላ”፣ “ጉሮ ወሸባዬ”፣ “ምንም አያኮራ”፣ “ሰላማችን ይፅና”፣ እና “ከጠላት አልኮል ተው ተከልከል” በተሰኙ አጫጭር በግጥም የተፃፉ ተውኔቶቹ መሆኑን ሌላው የአዲስ አበባ መካነ አዕምሮ የቴአትር ጥበብ መምህር ዳኜ አበበ “የኢትዮጵያ ቴአትር ልደት - እድገት” በተባለ መፅሀፉ አስነብቧል። ማቴዎስ በቀለ በአጫጭር ድራማዎች ባገኘው ስኬት እና ተቀባይነት በመበረታታት በቀጣይ አመታት በ1941 እና 1943 የላቀ የቅኔ እና ስነፅሁፍ ችሎታን የሚፈታተነውን ነገር ግን በኢትዮጵያዊያን ልሂቃን ዘንድ በስፋት የሚተገበረውንና የእውቀት መለኪያ የሆነውን በግጥም መፃፍን በይዘት እና ቅርፅ በማሳደግ ገፍቶበታል። “እሁድ ለሰኞ አጥቢያ”፣ “የሰው ስህተት የቸርነት ጉልበት”፣ “የማታ ማታ ያ እውነቱ ረታ”፣ “የኤርትራ ጀግኖች ሙያ”፣ “ጋብቻ ከበረ”፣ እና “እርሻ የኢትዮጵያ ጋሻ” የተሰኙት ረጃጅም ተውኔቶች ሙሉ በሙሉ በግጥም የተፃፉ የማቴዎስ የጥበብ ውጤቶቹ ናቸው።

ለኢትዮጵያ ቴአትር በስጦታነት የተበረከተው ይህ ሁለገብ ከያኒ ከ1941 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር ተቀጥሮ ይሰራ ነበር። ለስድስት አመታት ያህል በቅጥር ሲሰራ ከቆየ በኋላ በመንግስት ጥላ ስር ሆኖ በህግጋት ታጥሮ መስራት ያስከተለው የጥበባዊ ነፃነት ጥማት ወይ ደግሞ ባልታየ መንገድ ጥበብን ማሳደጊያ እና ተደራሽ ማድረጊያ መንገድ ውል ብሎት፤ ብቻ ለጊዜው በጥናቴ ባልደረስኩበት ምክንያት በ1946 ዓ.ም ከሀገር ፍቅር ቴአትር በመልቀቅ “አንድነት የቴአትር ቡድን” የሚል የቴአትር ድርጅት አቋቋመ። በነገራችን ላይ አንድነት የቴአትር ቡድን በኢትዮጵያ እስካሁን ባለው የ100 አመታት የቴአትር ታሪክ ውስጥ ካሉ በጣት ከሚቆጠሩ የግል የቴአትር ተቋማት መካከል የመጀመሪያው እና ፈር ቀዳጁ ነው።

አንድነት የቴአትር ቡድን የማቴዎስን የቴአትር ጥበብ ልዕለ ሀያልነት ፍንትው አድርጎ ያሳየ ታሪክ ፅፎ አልፏል። እንደ መምህር ዳኜ ገለፃ ድርጅቱ ባልታወቀ ምክንያት በ1956 ዓ.ም እስከፈረሰበት እለት ድረስ በመላው የሀገሪቱ ገጠራማ ክፍሎች በመዘዋወር የቴአትር ጥበብን አስተዋውቋል፣ ህዝብን በፈንጠዝያ ምናብ ውስጥ ከቶ ለህይወታቸው ተጨማሪ ጣዕምን ሰጥቷል፣ የቴአትር ጥበብ ተደራሽነትን በእጅጉ አስፋፍቷል፣ የቴአትርን የችግር ፈቺነት እና ማህበራዊ አንቂነት አቅም አጎልብቷል፣ ህዝብን አስተምሯል፣ የቴአትር ጥበብን በሚገባ አሳድጓል።

ማቴዎስ በ1958 ዓ.ም ለታሪክ እና ለመጪው ትውልድ መማሪያነት ያገለግል ዘንድ ባሳተመው “ቴአትር እና ዘፈን በኢትዮጵያ” በሚለው መፅሀፉ ውስጥ ስለ ቴአትር ቡድኑ የሚከተለውን አስፍሯል፡

... አንድነት የቴአትር ቡድን ለሀገር ያደረገውን እርዳታ ለመግለፅ የሞከርን እንደሆነ በመቶ የሚቆጠሩ ገፆች ይፈጅ ይሆናል ... አንድነት የቴአትር ክፍል በአዲስ አበባ እና በየጠቅላይ ግዛቱ እየተዘዋወረ የቴአትር እና የሀገር ጨዋታዎችን ማሳየት የጀመረ ሲሆን ከ’ሱ በፊት ይህንን የመሰለ መልካም አርአያ የሚፈፅም እንኳንስ የግል መንግስታዊም ድርጅት አልነበረም። አንድነት የቴአትር ክፍል እንደዛሬው መጓጓዣ በብርቱ ሳይሰለጥን በሀገሪቱ ከጠረፍ እስከ ጠረፍ እየተዘዋወረ ቴአትርና ዘፈን አሳይቷል።

አንድነት የቴአትር ቡድን በ1940ዎቹ እና 50ዎቹ ኢትዮጵያ ከነበረችበት የእድገት ደረጃ፣ የማህበረሰብ ንቃት እና የቴአትር ጥበብ መስፋፋት አንፃር ሊገጥሙት የሚችሉትን ችግሮች በተለይ የዚህ ዘመን የቴአትር ባለሞያዎች በአሁኑ ግዜ ካለው ህልቆ መሳፍርት ችግር አንፃር መገመት አይከብዳችሁም። የዛሬዎቹ የቴአትር አርበኞቻችን የምትጋፈጡት ችግር ታዲያ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በመዲናችን አዲስ አበባ ያሉ ችግሮችን ብቻ ነው የእነ ማቴዎስ ዘመኖቹ ግን በመላው ሀገሪቱ ያሉ ችግሮች በቀጥታ ያገኟቸው ነበር። በአዲስ አበባና ክፍላተ ሀገራት ዙረታቸው ከገጠሟቸው እጅግ በርካታ ፈተናዎች መካከል ህይወታቸውን አደጋ ላይ የጣለውን አንዱን ብቻ በዋቢነት ላንሳላችሁ። ይህ ገጠመኝ የተከሰተው የቴአትር እና ዘፈን ጨዋታቸውን ለማሳየት ኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት ‘ገባ/ቶልቸራ’ የሚባል አካባቢ በሄዱበት ወቅት ነው።

... ገባ ጅረት ሲወርዱ ቁልቁለቱ፣ ሲወጡ ደግሞ ዳገቱ በጣም አስፈሪ ስለሆነ እኛም ከመኪና ወርደን በእግራችን ማዝገም ጀመርን። የምንጓዝበት የነበረው ፊያት ትሬንታ ኳትሮ ቁልቁለቱን ወርዶ ዳገቱን ሲጀምር በግራ በኩል ያለው የመንገዱ ጠርዝ ተንዶ መኪናው በመተኛቱ እቃዎቻችን እየተገለባበጡ ገደል ገቡ። እመኪናው ላይ ብንኖር ግን የሚተርፍ አለ ለማለት ፈፅሞ አይቻልም። የመኪናው ግማሽ አካል ከገደሉ አፋፍ ላይ እኩሌታው ደግሞ አውራ ጎዳናው ላይ ሆኖ ከበረሀው ውስጥ አንድ ቀንና አንድ ሌሊት ካሳለፍን በኋላ ቁጥራቸው ከሀያ በላይ የሚሆኑ ከጎሬ ወደ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ጎሬ የሚጓዙ ከባድ መኪናዎች በየሰአቱ ደረሱና ከስንቃቸውም ተከፋፍለን፣ ችግሩ ያነሰ በመሆኑ በገደሉ በኩል የተኛውን የመኪና አካል በ58 ሰዎች ጉልበት እና ዘዴ ለአንድ ቀን ሙሉ ተቃኝቶ እኛንና የመኪናውን ባለቤት እግዜር ስለረዳን ጉዞ ቀጠልን።

ማቴዎስ በአንዳንድ ድርሳናት ዘንድ 27 በሌሎች ደግሞ 34 ረጃጅም እና አጫጭር ተውኔቶችን እንደፃፈ፣ እንዳዘጋጀ እና በአንዳንዶቹም ላይ እንደተወነ ተፅፏል። ቁጥሩ የትኛውም ቢሆን በ’ኔ ግላዊ ምልከታ ያልተሰነዱት ስለሚበልጡ ከላይ ከተጠቀሱት ቁጥሮች ቢበልጥ እንጂ ያነሰ አይሆንም። ጊዜ እና የመረጃ ቋቴ ቢፈቅድ ከስር የምዘረዝራቸውን ማቴዎስ ከሰራቸው ቴአትሮች መካከል ጥቂቱን በበለጠ ጥልቀት ተንትኜ ባቀረብኩ ደስ ባለኝ ነበር። ነገር ግን አንደኛ በዚህች ምጥን ውስጥ በወፍ በረር ጠቃቅሶ ከማለፍ በላይ መግፋት አይፈቀድልኝም ሁለተኛ ልለፍ እንኳን ብል ስለተውኔቶቹ ጭብጥ፣ ተዋንያን፣ የዝግጅት ሂደት፣ ዘውግ፣ እና በአቅርቦቱ ወቅት ስልነበረው ነገር ተሰንዶ የተቀመጠ ማስረጃ ስለሌለ ከአፋዊ ሀሳቦች እና ግምታዊ መላምቶች በዘለለ በቂ ነገር ማግኘት የማይቻል ነው (እንዲህ አይነት ጠለቅ ያለ መረጃ እንኳን በቀደሙት ላይ በአሁኖቹም ላይ ማግኘት እጅግ አዳጋች እየሆነ ነውና የሚመለከታችሁ ልብ ብትሉልኝ)። ማቴዎስ ከአንድነት የቴአትር ቡድን መፍረስ በኋላ ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር በመመለስ እስከ 1956 ዓ.ም ድረስ ለአምስት አመታት ያህል የጥበብ ስራዎቹን ሲሰራ ቆይቶ ነብይ በሀገሩ አይከበርምና በጀት የለንም በሚል ምክኒያት ተቀናሽ ተደርገ። ለክብሩ በማይመጥን፣ ለውለታው በማይገባ፣ እና ከሚያደርገው አስተዋፃኦ ጋር በፍፁም በማይነፃፀር መልኩ ከቴአር ቤቱ እስኪባረር ድረስ ካቀረባቸው ቴአትሮች መካከል ጥቂቱ፡ “እድሜ ልክ እስራት”፣ “አስናቀች”፣ “ላቀች በምስራቅ ዘለቀች”፣ “ህግና ፖሊስ”፣ “ኢትዮጵያ ይህቺ ናት”፣ “ክራርና ፈትለሽ ልበሽ”፣ “የሚስጥር ዘበኛ”፣ “ህዳር 28 ቀን 1928 ዓ.ም”፣ “ልጃገረድ አስር ያጭሽ አንድ ያገባሽ”፣ “እማሆይ አለሚቱ”፣ “ጤናውን የሚወድ ባ’ልኮል አይንደድ”፣ “ሎሚ ኮለል ብላ ወረደች በደጅ”፣ “አዳኞች ከበረሀ ሲመለሱ”፣ “ደባ እራሱን ስለት ድጉሱን”፣ “እኔና ገንዘቤ”፣ “አትዋሺ ብቻ”፣ “ቃልህን አምንሀለሁ ሀገርህን ውደድ”፣ “እኔና አንቺ ደህና”፣ “ተያይዞ ገደል”፣ “ወድቃ የተገኘች ልጅ”፣ “እንዳሻው ተምትሜ”፣ “የየካቲት እልቂት”፣ “ጋብቻ ከበረ”፣ “ኢትዮጵያ”፣ “የመንፈስ ብርታት”፣ “የሰው ስህተቱ የቸርነት ጉልበቱ”፣ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር”፣ “ጉሮ ወሸባዬ”፣ “ምንም አያኮራ”፣ “ሰላማችን ይፅና”፣ “ወንድሙና ጠላቱ” ናቸው። እነዚህ ተውኔቶች ታዲያ ግማሹ በግጥም ገማሹ ደግሞ በዝርው የተፃፉ ናቸው። በዘውግ ደረጃም የተወሰኑቱ ጭፍግ ሲሆኑ የተወሰኑት ደግሞ ፍግ ናቸው። የሚያነሱት ሀሳብም ማህበራዊ፣ ታሪካዊ፣ ስነምግባራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮችን ነበር። ቅርፃቸውም የተለያየ ነበር።

ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ጥቂት ፀሀፍት መካከል አምራች ፀሀፊ የሚባለው ማቴዎስ በስራው ላይ ቀልድ የሚያውቅ አልነበረም። ከምንም በፊት የቆመለትን፣ የሚታገልለትን፣ የሚሰዋለትን አላማ ያስቀደመ መንፈሰ ጠንካራ ሰው ነበር። የቴአትር ስራ ሲሰራ በቴአትሩ ቡድን መካከል የሚፈጠረውን ሀተካሮ ሁላችሁም የምታውቁት ነው። በተለይ ደግሞ የቴአትር አዘጋጆች በተዋንያን የምግባር ብልሹነት የሚደርስባችሁን ብስጭት፣ የምታሳልፉትን መራር ጊዜ የምታውቁት ነው። ማቴዎስ እንዲህ እኩይ ምግባር ያላቸው ተዋንያን ሲገጥሙት ምን ድንቅ ችሎታ ቢኖራቸው የበሉበትን ወጪት ሰባሪዎች ናቸውና የሚታገስበት ምንም አይነት ምክንያት አልነበረውም። ፍላጎት ያለውን ሰው አምጥቶ ወደ ድንቅ ተዋናይነት መቀየር እንደሚችል በራሱ እጅግ ይተማመን ነበር (በነገራችን ላይ ማቴዎስ በቀል ግሩም አስተማሪ ነበር። የሀገር ፍቅር ሌላው ሁለገብ ከያኒ ኢዮኤል ዮሀንስ የማቲዎስ በቀለ ተማሪ ነበር። የምምህሩን ብቃት ለመለካት የተማሪውን አቅም ተመልከት አይደል ነገሩ?) ለዚህም ማሳያ እንዲሆን በእኩይ ምግባር ያላቸው አድመኛ ተዋንያን እና የቡድን አባላት ላይ ከወሰዳቸው የማያዳግሙ እርምጃዎች መካከል በመምህር ፋንታሁን እንግዳ የተፃፉትን ሁለቱን ላንሳላችሁ። አንድነት የቴአትር ቡድን በአንድ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር የቴአትር እና ሙዚቃ ድግስ ለማቅረብ በሄደበት ወቅት ሴት ተወዛዋዦች “መቼም ሴት ተወዛዋዥ ከየትም አያመጣም” ብለው አደሙና አንሰራም አሉ። ቆራጡ ማቴዎስ ታዲያ እንዳሰቡት መለማመጡን ትቶ የወንዶቹን ፂም አስላጭቶ፣ ቀሚስ አልብሶ በሴቶቹ ቦታ ተክቶ አሰራ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ወንዶች ተዋንያን በሚገባቸው ልክ ሳይሆን እንደው ለነገሩ የግብር ይውጣ ሲሰሩ ማቴዎስ ከመድረክ ያባርርና እራሱን በተዋንያኑ ቦታ በመተካት ሰርቷል።

ማቴዎስ በቀለ ከፃፋቸው ተውኔቶች መካከል እጅግ ረጅሙ “ህግና ፖሊስ” የተሰኘው ነው። ይህ ቴአትር ለ16 ሰአታት ለሶስት ሳምንታት በተከታታይ የታየ እጅግ ረጅም ቴአትር ነው። አንዳንድ አጥኚዎች ይህ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ ረጅሙ ቴአትር ነው ይላሉ ነገር ግን በደቀመዝሙሩ ኢዮኤል ዮሀንስ የተፃፈው “ዘጠኝ ፈተና ያለፈ ጀግና” ለ10 ሳምንታት የታየ በመሆኑ የረጅም ቴአትር ሪኮርድን የሚይዘው ኢዮኤል ዮሀንስ ነው። የማቴዎስ “ህግና ፖሊስ” በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል። ስለዚህ ታላቅ ሀገር አፍቃሪ የሀገር ፍቅሩ ኢትዮጵያዊ የጥበብ አምድ ተጨማሪ የምትሉት መረጃ ካላችሁ በሀሳብ መስጫው ላይ አጋሩን እኔ ለዛሬ በዚሁ ላቁምና የባለሪኮርዱን ምጥን ታሪክ ላሰናዳ። ቸር ይግጠመን።


84 views0 comments

コメント


bottom of page