top of page
Search
  • mastu89

ትምህርት ለሁሉም!

Updated: Nov 22, 2021

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ1948 ጀምሮ “በአለም አቀፍ የሰባዊ መብት ድንጋጌ”፣ “በአለም አቀፉ የምጣኔ ሀብት፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ስምምነት”፣ “በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውም አይነት መገለልን በሚቃወመው አለም አቀፍ ስምምነት”፣ “በአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ቻርተር”፣ “በህፃናት መብት ስምምነት፣ በአለም አቀፉ የትምህርት ለሁሉም አዋጅ”፣ “በዳካሩ ፍሬም ወርክ ፎር አክሽን፡ ትምህርት ለሁሉም”፣ “በአካል ጉዳተኞች መብት ስምምነት”፣ “በተባበሩት መንግስታት ትምህርትን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች የማዳረስ ስምምነት”፣ እና በሌሎችም አለም አቀፍ ስምምነቶች ውስጥ ትምህርት መሰረታዊ የሰው ልጅ መብት መሆኑ ተደንግጓል። ትምህርት እንደ የሰው ልጆች መሰረታዊ መብት ለምን ተቆጠረ? ከዘመናችን በፊት የነበሩትን የአባት አያቶቻችንን ትውልድ መለስ ብለን ብንቃኝ ሀገርን ያለ አንዳች ‘ዘመናዊ’ ትምህርት ቀጥ አድርገው አስተዳድረው፣ ባህላችንን፣ ቋንቋችንን፣ እምነታችንን አቆይተው፤ የማይደፈሩ ከሚመስሉ አውሮፓዊ ሀይሎች ጋር እጅግ ኋላ ቀር በሚባል መሳሪያ ተዋግተው፣ የጥይት ትንኳሽ፣ የመርዝ ጋዝ፣ የጦር ጀቶች የእሳት ዝናብ፣ ችጋር እና ረሀብ ሳይበግራቸው ይህቺን ድንቅ ሀገር አስረክበውናል። ዛሬም በየአካባቢያችን ከሀብት ማማ ላይ የተቀመጡ አድራጊ ፈጣሪ የጎበዝ አለቆች ቀለም ያልዘለቃቸው በመሆናቸው ብዙዎቻችን “እኔ እናቴ ስትረግመኝ ነው ፈተና ያለፍኩት፣ ያኔ እንደ እከሌ ወድቄ ሊስትሮ ወይም ጀብሎ ጀምሬ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የት በደረስኩ” የሚሉ ቀልድ አዘል መልእክቶችን ከወዳጆቻችን ጋር በየመዝናኛ ቦታው እንጋራለን። ዛሬ ዛሬ እንደውም በተቃራኒው የተማሩቱ የመንግስት ቅጥረኛ በመሆን የዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋዮች እና የዝቅተኛው ኑሮ መደቦች በሀገሬው አጠራር ‘አኗኗሪዎች’ ነን። ታዲያ ትምህርት የግለሰብን ህይወት ቀይሮ ሀገርን ካልጠቀመ ከላይ በተጠቀሱት የአለም መድረኮች በሙሉ ‘የሰው ልጅ መሰረታዊ መብት’ ተብሎ ለምን ተሰየመ? እነዚህ መንግስታት ምን ሽው ብሏቸው ነው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ “ለምን?” አንልም።

በትምህርት የመሰረታዊ መብትነት ድፍየና መሰረት ትምህርት የሰው ልጆች በምድር ላይ የተፈቀደላቸውን ግዜ ሲኖሩ እያንዳንዷ እለት የምትለግሳቸውን መልካም አጋጣሚዎች በሚገባ አጣጥመው፣ የሚያጋጥሟቸውን መሰናክሎች እንደ መልካም ድልድይ ተጠቅመው ጥራት ያለው ህይወት እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። ትምህርት የሰው ልጆች ሌሎች መሰረታዊ የመኖር መብቶቻቸውን በአግባቡ እንዲያውቁ እና እንዲያስከብሩ የሚያስችል ብቸኛው መንገድ መሆኑ በበርካታ ጥናቶች እና ህያው ምስክሮች ተረጋግጧል። ይህ “ትምህርት ለሁሉም” እየተባለ የሚደሰኮርለት ሀሳብ እውነት በተጨባጭ ምን ፋይዳ አለው? የሚል ጥያቄ ቢነሳም ክፋት የለውም ምክንያቱም ምላሹ ቀላል ነው። ትምህርትን በአግባቡ ለተጠቀመበት ድህነት ከሚባል ወረርሺኝ ማምለጫ፣ ከማህበራዊ መድሎ መፅጃ፣ ሴቶች እና ህፃናቶቻችንን ማነቃቂያ፣ እና የሰው ልጅን መክሊት ማውጫ መንገድ ነው። ከዚህም ባሻጋር ዘላቂ ልማትን በማሳካትና የሀገርን የምጣኔ ሀብት ደረጃ በማሳደግ የህዝቦችን ሰላም ማረጋገጫ ቁልፍ የአብሮነት መሰረት ነው። የተማረ ህዝብ ከጥሬ ስሜት ወጥቶ ነገሮችን በአመክንዮ ማመዛዘን ይችላል። ለሚመጡበት ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮአዊ አደጋዎችም ተገቢውን ምላሽ በማያዳግም መልኩ ለመስጠት የሚያስችል ህዝባዊ አቅም ይገነባል።

ይህ ሰብአዊ መብት በተፈጥሮ የሚሰጠን ወይስ ከሆነ አካል የሚለገሰን?

የሰው ልጅ በተፈጥሮው አካባቢውን፣ በአካላቱ ላይ የሚካሄዱ ለውጦችን እና በተፈጥሮአዊ እድገቱ ውስጥ ያሉ ለውጦችን ሰው በመሆኑ ብቻ በተፈጥሮ ይማራቸዋል ነገር ግን የሰው ልጅ የፈጠረውን ‘ትምህርት’ በቤተሰቡ፣ በሀገሩ፣ አሊያም በሆነ ረዳት አማካኝነት ካልሆነ በስተቀር ሊማረው አይችልም። ጉዳዩን እንደ ህዝብ ካየነው ደግሞ ትምህርትን ማቅረብ ያለበት የህዝቡ አስተዳዳሪ መሆኑ አያጠያይቅም። አስተዳዳሪው አካል ቢያንስ ቢያንስ ትምህርትን ማቅረብ፣ ተደራሽ ማድረግ፣ ከአካባቢያዊ ሁኔታ እና ልማድ አንፃር ተቀባይ እና እንደየሁኔታው ሊስማማ የሚችል የማድረግ ግዴታ አለበት። የሀገራችን ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ የሚገባው እንግዲህ እዚህ ጋር ነው። በርግጥ ለዚህች ምጥን ፅሁፍ መነሻ የሆነኝም ይኸው ጉዳይ ነው። ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ግን በአለማችን ምን ያክል ሰዎች የትምህርትን መሰረታዊ መብት ተነፍገው እንደሚኖሩ ልንገራችሁ። በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የማህበራዊ እና ባህላዊ ተቋም ጥናት መሰረት ከ263 ሚሊየን ህፃናት እና ወጣቶች በላይ የትምህርት መብትን ተነፍገዋል። ከዚህ ቁጥር ውስጥ ደግሞ እጅግ ከፍተኛወን አብላጫ የሚወስዱት ከሰሀራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ህዝቦች ናቸው። ኢትዮጵያን ጨምሮ ማለት ነው።

ኢትዮጵያችን ውስጥ በፖሊሲ ደረጃ ከጥራት በፊት መዳረስን ተቀዳሚ ኢላማ በማድረግ ሲሰራ ቢያንስ ሶስት አስርት አመታት አልፈዋል። በትንሹ ሶስት ትውልድ ማለት ነው። በአሁኑ ግዜ ሀገሪቷን እየመራት ያለው እና ለመረከብ በተጠንቀቅ ላይ ያለው ትውልድ ከጥራት ተደራሽነትን ባስቀደመ ፖሊሲ ውስጥ ተጠፍጥፎ የተሰራ ነው። ለዚህም ይመስላል በሚሊኒየሙ መባቻ ‘አንድ ዲግሪ ያለው ሰው ቢያንስ በልቶ ማደር አለበት’ በሚል መርህ ምሩቃን በጠቅላላ ያለሞያቸው በጥቃቅን እና አንሰተኛ እየተደራጁ የእለት ጉርሳቸውን እንጂ ዘላቂ የአእምሮ ጥያቄያቸውን ቸል ብለው ሲፍጨረጨሩ የኖሩት፤ እየኖሩም ያሉት። ለነገሩ አንድ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የተማረ ወጣት ወደፊት የሚሰማራበት የሙያ መስክ ወይም ግላዊ ተሰጣኦው በመንግስት በእጣ ተወስኖለት በሚማርበት ሀገር ከምርቃት በኋላ ስለ ሙያ ክብር እና ጥቅም የሚከራከር ትውልድ መጠበቅ ሞኝነት ነው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለፋችሁ ወይም በአሁኑ ግዜ በተለያየ ደረጃ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የምትገኙ አንባቢዎቼ በተለይ የምለው ግልፅ ብሎ እንደሚገባችሁ አልጠራጠርም። የሆነው ሆኖ ስለከፍተኛ ትምህርት ‘መራቀቁን’ (ምን ያመፃድቅሀል? ዋናው ገብቶ መመረቅ፣ ቤተሰብና ዘመድን መቀፈል፣ ቺክ መጥበስ፣ የምረቃ ድግስ መብላት፣ የዲግሪ ፎቶ ግድግዳ ላይ መስቀል ከዛ ስራ ፍለጋ በሚል ፈለጣ ማጧጧፍ፣ የተለያዩ የቢዝነስ ሀሳቦች አሉኝ በማለት የፈለጣ ዲግሪን ከፍ ማድረግ፣ እምቢ ካለ ድንጋይ ይዞ ለአመፃ መነሳት አይበቃም? የምትሉ እንደማትጠፉም አምናለሁ) ለጊዜው እንተወውና እስቲ መሰረታዊ የትምህርት ጉዳይን ከኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል አንዱ የሆነውን የሙርሲ ብሄረሰብን ዋቢ በማድረግ እናውጋ።

የሙርሲ ብሄረሰብ አንዳንዶቻችሁ እንደምታውቁት (መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የደቡብ ኦሞ ቴአትር ኩባንያ https://www.southomotheatre.com/ ጥናት ተሳታፊ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና በከተማዋ የሚገኙ ነዋሪዎች ሙርሲ ብሄረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን እንኳን እንደማያውቁ አረጋግጧል) በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ ከሚገኙ አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደሮች መካከል አንዱ ብሄረሰብ ነው። ለተጨማሪ መረጃ፡ (https://www.mursi.org/)። ይህ ብሄረሰብ ታዲያ በሀገር በቀል እውቀቱ ብቻ እየተመራ ከቀሪው አለም ስልጣኔ ተገልሎ በርካታ መቶ አመታትን ኖሯል። ዛሬ አለም በተለያዩ የስልጣኔ ደረጃዎች ተራቅቃ፣ በእውቀት በልፅጋ ባለችበት ወቅት አንዳንድ የምዕራቡ አለም ጎብኚዎች ‘የሰው ልጅን የቅድመ ታሪክ ዘመን አሊያም እጅግ ኋላ ቀር የነበረውን የሰው ልጅ አኗኗር’ በአካል መመልከት ሲፈልጉ ቅድሚያ የሚሰጡት ቦታ የሙርሲ ምድር ሆኗል። ጥቂት የማህበረሰቡ አባላት ባገኙት የትምህርት እድል አማካኝነት ‘ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊታቸው’ የመላቀቅ እርምጃ ቢጀምሩም በምዕራባዊያን ‘ምሁራን’ የሁለት ጎራ ማለቂያ የሌለው ክርክር፣ በሀገሪቱ ቸልተኝነት እና ይህ ድርጊት በሚያስገኝላቸው ጥቂት ዳረጎት ምክንያት በለውጥ እና በቀደመው መንገዳቸው መሀል ቆመዋል። ባህል በርግጥ በባህሪው ቋሚ አይደለም። ማህበረሰቡ ይጠቅመኛል ባለ ጊዜ ሊፈጥረው፣ ሊያሳድገው እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊያሸጋግረው አይጠቅመኝም ባለ ጊዜ ደግሞ ሊያጠፋው የሚችል ማህበራዊ ሀብት ነው። የሙርሲ ብሄረሰብም እንደባህል እና የማንነት መገለጫዎቹ ቆጥሮ እስከዛሬ ያኖራቸው እና ወደፊትም ለልጅ ልጆቹ የሚያወርሳቸው፣ ባላሰፈለገው ጊዜ በማህበራዊ አወቃቀሩ ታግዞ የሚያጠፋቸው እና የሚያሻሽላቸው ትውፊቶች ያሉት ምሉዕ ማህበረሰብ ነው። ዳሩ ግን ዛሬ ምስጋና በሰው ልጆች ላይ መቆመር ለማይደክማቸው ምዕራባዊያንና ልክ ህዝቡ እንዳልሆነ ሁሉ ችላ ላለው የኢትዮጵያ መንግስት ይሁንና የሙርሲ ማህበረሰብ ሀገር በቀል እውቀቶቹን ጠብቆ፣ የማያስፈልጉትን ደግሞ በትምህርት በመታገዝ ለይቶ አውቆ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በህይወቱ ላይ የመወሰን መብቱን ተነጥቋል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን በአካባቢው ላይ ‘ከአንገት በላይ’ በሚያስብል መልኩ የተተገበረው የትምህርት አቅርቦት ስርአት ነው።

የሙርሲ ማህበረሰብ ከፊል አርብቶ አደር በመሆኑ በአንድ ቦታ ረግቶ ሊኖር የሚችለው ግፋ ቢል ለሁለት አመታት (ሁለት የምርት ወቅት) ብቻ ነው። ታዲያ ለዚህ ህይወቱን ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ላይ ለመሰረተ ማህበረሰብ ምን አይነት መንግስታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ አገልግሎቱን የተሳካ እና ከልብ የመነጨ ያደርገዋል? የትምህርት ስርጭቱ በምን መልኩ መከወን አለበት? ለጥያቄዎቻችን አጭር መልስ ለማግኘት እስካሁን በመንግስት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተደረጉትን የትምህርት አቅርቦት ሙከራዎችን በወፍ በረር እንመልከት፡ በሙርሲ መዲና ማኪ ኤስ አይ ኤም በተባለ የሚሲዮን ድርጅት እና በጃፓን ህዝቦች ድጋፍ ወደ ሶስት ሚሊየን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር ወጥቶበት የተገነባው ትምህርት ቤት እጅግ ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎ የአካባቢው ነዋሪ በተለመደ የኑሮ ዘይቤው ሳቢያ ወደ ሌላ ቦታ ሲዘዋወር የተገነባው ቤት ባዶውን ቀረ። የኢትዮጵያ መንግስትም ትምህርትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ባለው ተነሳሽነት ከኢትዮጵያዊያን ግብር ላይ በመቀነስ እጅግ በርካታ ትምህርት ቤቶችን የገነባ ቢሆንም አንዳቸውም የታሰበውን ግብ መምታት አልቻሉም። ምክንያቱም የህዝቡን አኗኗር ያማከለ እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ከህዝቡ ጋር ያልተስማማ በመሆኑ ነው። በተመሳሳይ በአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት እና በፓክት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ ትምህርት ቤቶችም እንዲሁ ባክነው የህያዊያን ሳይሆን የመናፍስት መፈንጫ ሆነው ቀርተዋል።

መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሙርሲ ትምህርት ነገር አሳስቧቸው ይህንን ሁሉ ከደከሙ ታዲያ ለምን ሳይሳካ ቀረ? መልሱ ቀላል ነው። አንዳቸውም ለሙርሲ ‘ይህ ያስፈልገዋል’ አሉ እንጂ ሙርሲዎችን ‘ምን ያስፈልጋችኋል?’ ብለው አልጠየቋቸውም። የትምህርት ቤቶቹ አለመሳካት ሙርሲዎችን እንደ ትምህርት/ እውቀት ጠል ማህበረሰብ አድርጎ ቢያስቆጥራቸውም ሙርሲዎች ግን ፀሀይ ወጥታ በጠለቀች ቁጥር ለእውቀት የሚባትቱ፣ ዘመናዊነትን የሚናፍቁ፣ ያሏቸውን እምቅ ሀብቶች በተሻለ መንገድ ሰንደው ለትውልድ ማሸጋገርን የሚሹ ህብረተሰቦች ናቸው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነንም ከላይ የተጠቀሱትን የከሸፉ ሙከራዎች በጥሞና የታዘበው የሙርሲው ተወላጅ ኦሊሰራሊ ኦሊቡዪ የጀመረው እጅግ አበረታች ፕሮጀክት ነው። የኦሊ ፕሮጀክት በአጭሩ ሲገለፅ “ተንቀሳቃሽ ትምህርት ለመላው ሙርሲ” ይባላል።

የኑሮ ሁኔታቸው እና ማህበራዊ አወቃቀራቸው ሙርሲዎችን በአንድ ቦታ ረግተው እንዳይኖሩ አድርጓቸዋል። ይህ ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው። ህዝቡ ለሺህ ዘመናት የኖረው በየወቅቱ ለም መሬትን እና ወንዝን ተከትሎ እየዞረ በአጭር ጊዜ የሚበቅሉ አዝዕርትን በመትከል እና ከብቶችን በማርባት ነው። ዛሬ ድንገት ተነስተን “ይህ የህይወት ዘይቤ አይጠቅምህምም አሊያም ከ’ንግዲህ እንዲህ ልትኖር አትችልም” ብለን ልናስቆመው አንችልም። ነገር ግን የህዝቡን ማህበራዊ እውነታ በማቀፍ የሚያስፈልገውን እውቀት እንዲያገኝ ማድረግ እንችላለን። ለዚህም አይነተኛው መንገድ ከማህበረሰቡ ጋር አብሮ እየተዘዋወረ ሊያስተምር የሚችል ስርአት መፍጠር ነው። ይህ መንገድ ለማንኛውም በትምህርት ዘርፍ ላይ ለተሰማራ ባለሞያ የሚጠፋ አይደለም። ምክንያቱም በስነ ትምህርት ቢጋር ውስጥ የተዘረዘሩ ‘ስኬታማ የማስተማሪያ መንገዶችን’ ሳያነብ በትምህርት መስክ ውስጥ የተሰማራ ሰው/ድርጅት ሊኖር አይችልምና። እንኳን ባህር ተሻግረው እነሱ አጣጥመውት ለሌላው/ለተበደለው የተመኙት፣ በሙያ ደረጃ የተራቀቁበት ምዕራባዊያን የትምህርት አቀንቃኞች ቀርቶ፤ እንኳን በዲግሪ ላይ ዲግሪ ጭኖ ለ85 በመቶ የሀገሪቱ ነዋሪ ‘እኔ አውቅልሀለሁ’ እያለ ለሚደነፋ የመንግስት ባለስልጣን ቀርቶ ትምህርት ባለፈበት ላላለፈው ለሙርሲው ተወላጅ እንኳን ይህ ሀቅ ፍንትው ብሎለታል።

ኦሊ አካባቢውን በትምህርት ለመለወጥ የተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤት ፅንሰ ሀሳብን ይዞ አጋዥ ፍለጋ እየኳተነ ይገኛል። በጉብኝት አጋጣሚ በሚያውቃቸው የውጪ ሀገር ዜጎች ጥቂት እርዳታ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል የመማሪያ መፅሀፍ በሙርሲ ቋንቋ አዘጋጅቷል። በሌላ አጋጣሚ ካገኛቸው ኢትዮጵያዊያን እና የውጪ ሀገር ዜጎች ጋር በመሆንም የሙርሲን ባህል ሊያስተዋውቅ፣ ሊያሳድግ፣ ሊሰንድ፣ ለቀሪው አለም እና ለመጪው ትውልድ ሊያስተላልፍ ብሎም የተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤት ስርአት የመዘርጋት ህልሙን ወደ ተግባራዊነት ሊያቀርብለት የሚችል የቴአትር እና ዘጋቢ ፊልም ፕሮጀክት እየሰራ ይገኛል። ስለ ፕሮጀክቱ ይዘት እና ደረጃ በሌላ ፅሁፍ እመለሳለሁ። ኦሊ ያለውን አቅም በሙሉ በማስተባበር ማህበራዊ ሀላፊነቱን፣ የአባትነት ግዴታውን ለመወጣት በኢትዮጵያ በተለይም በደቡብ ክልል ከሚገኙ መካነ አዕምሮዎች (www.wku.edu.et www.jku.edu.et) ጋር በጥምረት እየሰራ ይገኛል። የትምህርት ጥማት በተለይ ከሰሀራ በታች ለሚገኙ ህዝቦች አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ የትምህርት አቅርቦት ችግር አዲስ ጉዳይ ባይሆንም እንዲህ አስተምሩን፣ አሳውቁን፣ መንገድ ምሩን የሚሉ ድምፆችን ችላ የምንለው እስከመቼ ይሆን? “ትምህርት ለሁሉም!” መፈክራችን ከወሬ በዘለለ ግዘፍ ነስቶ በልጆቻችን መለወጥ፣ በሀገራችን እድገት ውስጥ መታየት የሚጀምረው መቼ ይሆን? አበቃሁ!


76 views0 comments
bottom of page