top of page
Search
southomotheatre

ውበት ሲለካ ...

Updated: Nov 22, 2021


የዛሬ ፅሁፌን ብዙዎቻችንን በሚያስማማ አንድ አባባል ልጀምር፡ “ውበት እንደተመልካቹ ነው”። ውበት እንደየተቀባዩ የተለያየ ደረጃ ተሰጥቶት ለአንዳንዶቻችን ፍፁም ውብ እና እንከን የለሽ የሆነው ውበት ለሌሎቻችን የአስቀያሚነት ምሳሌ የሚሆንበት አጋጣሚ እጅግ ብዙ ነው። ውበትን በውጫዊ እና በውስጣዊ መለኪያዎቹ በመመዘን ‘አንደኛው ከሌላው ይበልጣል’ የሚሉ ማብቂያ የሌላቸው ሙግቶችን በተደጋጋሚ መስማትም አዲስ ነገር አይደለም። የውበት ነገር ከግላዊ ስሜት እና መነካት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው በመሆኑ በአለም ላይ ላሉ ነገሮች ማማር እና ማስጠላት መመዘኛው እንደ አሻራችን የሚለያየው የእይታ መነፅራችን ብቻ ነው። ለዚህም ነው ‘ውበት እንደተመልካቹ ነው’ የሚለው አባባል ሁላችንንም የሚያስማማ አለም አቀፍ ድፍየና የሆነው። በዚህች አጭር ፅሁፍ የሙርሲ ልጃገረዶች የውበት መገለጫ ከሆኑት የከንፈር ላይ ሸክላ፣ የጆሮ ዝልዘላ፣ የሰውነት ቀለም፣ የሰውነት መበጣት፣ የአንባር፣ የአልቦ እና የአንገት ሀብል ድርድር መካከል ስለ ከንፈር ላይ ሸክላ በጣም በጥቂቱ አጫውታችኋለሁ። ስለሌሎቹ የውበት መገለጫዎቻቸው በሌላ ፁሁፍ እመለስበታለሁ።

ለሙርሲ ልጃገረድ ውበት ማለት እጅግ ውድ የአካል እና የመንፈስ ዋጋ የሚከፈልበት፣ በማህበረሰቡ ውስጥ መኖራቸውን የሚያረጋግጡበት የህይወታቸው ቁልፍ ነገር ነው። አንዲት የሙርሲ ልጃገረድ አስራ አምስት ወይም አስራ ስድስት አመት ከሞላት በኋላ በተፈጥሮአዊ ሂደት የህፃንነት ዘመኗ አብቅቶ ዳሌዋ ሰፋ፣ አጎጠጎጤዋ ብቅ ብቅ፣ ድምፁዋም ቀጠንጠን ማለት ይጀምራሉ። ምንም እንኳን የትዳሯ ነገር ገና በህፃንነቷ በቤተሰቧ አማካኝነት የተወሰነ ቢሆንም የመንደሩን ጎረምሶች ምራቅ ማስዋጧ ግን አይቀርም። እሷም ሰው ናትና የግል ፍላጎቷን መከተል፣ የሚማርካትን ወንድ ማማተሯ የሚቀር አይደለም። ወጣቷ መጎምራት ስትጀምር ታዲያ እናቷ አሊያም አሳዳጊዋ የውበቷን ነገር ‘በጄ’ ማለት ቀዳሚ ተግባሯ ነው። ይህች እናት ወይም አሳዳጊ የልጃገረዷን የሴትነት ጉዞ የታች ከንፈሯን በማሰንጠቅ ታሰጀምራለች። የከንፈር ስንጠቃው ሲካሄድ ህመሙ በጥልቀት እንዳይሰማት እጅግ የሳለ ቢላዋ ተመርጦ የታች ከንፈሯ በክብ ቅርፅ ይሰነጠቃል። የተሰነጠቀው ከንፈር ቀዳዳ ሰፊ እንዲሆን ከሁለት እስከ ሶስት ሳንቲ ሜትር እንጨት ይደረግበታል። ይህ እንጨት ቁስሉ እስኪደርቅ ድረስ ስፋቱ እየተጨመረ ይሄዳል። ምክንያቱም ሰፊ የከንፈር ቀዳዳ ያላት የውቦች ሁሉ ውብ ናትና።

የሙርሲ እናቶች ባላቸው የሀገር በቀል እውቀት የወጣቷን ህመም እንዲሁም ቁስሉን ከመመርቀዝ ወይም ከአላስፈላጊ ብክለት ለመከላከል የሚያስችላቸውን ባህላዊ መድሀኒት ቀምመው ይቀቧታል። ቁስሉ ለመድረቅ ከሶስት እስከ ስድስት ወራት ድረስ ቢፈጅበትም ስንጠቃው የተካሄደው በፍፁም ፍላጎቷ ላይ ተመስርቶ ስለሚሆን ከህመሙ ይልቅ የቁስል ጊዜው አብቅቶ በከንፈሯ ልክ የተሰራውን ሸክላ አድርጋ አጊጣ እስክትታይ ያለው ጊዜ ቶሎ አልደርስ ማለት የበለጠ ያማታል። የሙርሲ ብሄረሰብ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ነው፣ ሁሉም ሰው እኩል መብት እና እድል ሊሰጠው ይገባል የሚል ጠንካራ ማህበራዊ አስተሳሰብ አለው። የከንፈር ስንጠቃውም ከትንሽ የአቻ ግፊት በዘለለ ከታላላቆች፣ ከእናቶች ወይም ከሀገር ሽማግሌዎች የሚመጣ ምንም አይነት ጫና የለበትም። ሙሉ በሙሉ የሚከናወነው በወጣቷ ፍላጎት እና የማማር ጉጉት ላይ ተመስርቶ ነው።

የከንፈር ስንጠቃን ምናልባትም እስካሁን ከሚከውኑ በአፍሪካ ከሚገኙ እጅግ ውስን ብሄረሰቦች መካከል አንዱ የሆነው የሙርሲ ብሄረሰብ በከንፈር ላይ ለሚደረግ ሸክላ ልዩ ትርጉም አለው። አንዲት ሴት ከንፈሯ ላይ ሸክላ አደረገች ማለት የውበትን ጥግ የተቆናጠጠች፣ ለሴትነት ወግ የደረሰች ነች ማለት ነው። የከንፈሯ ላይ ሸክላ በሰፋ ቁጥር አማላይነቷ፣ ውበቷ እና ተፈላጊነቷ በዛው ልክ ይሰፋል። ለዚህም ታዲያ ልጃገረዷ ቁስሉ ከደረቀላት በኋላ አጠቃላይ ስፋቱ እስከ አስራ ሁለት ሳንቲ ሜትር የሚደርስ ሸክላ የታች ከንፈሯ ውስጥ ታደርጋለች። ሸክላው ያለምንም ችግር እንዲገባም ነፃ በሆነችባቸው ግዜያት ከንፈሯን በእጇ በማሸት ወይም ‘ማሳጅ’ በማድረግ ፤ ህፃን ልጅ ካላት ደግሞ ልጇ እንዲጫወትበት በመፍቀድ የበለጠ ትለጥጠዋለች። ከንፈሯ አንድ ጊዜ ተለጥጦ በልኩ የሆነ ሸክላ ከገባለት ልክ ዘመነኛ ሴት ረዥም ተረከዝ ያለው ጫማ አድርጋ ስትሄድ የሚሰማትን ህመም ያክል እንኳን አይሰማትም።

ከንፈር ላይ ሸክላ ማድረግ ማለት ከውበት በተጨማሪ የወላድነት ማረጋገጫም ነው። በሁሉም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ እንዲሁም በቀሪው አለም ወላድነት ያለው ዋጋ ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው። ይህ በልዩነት በሙርሲዎች ዘንድ የምዘወተረው የከንፈር ላይ ሸክላ ቀኑን ሙሉ ወይም ለአዘቦት አይደረግም። ያላገቡ ልጃገረዶች በአካባቢያዊ ስብሰባዎች፣ በልዩ ልዩ በአላት፣ በጭፈራ ቦታዎች (በነገራችን ላይ በጭፈራ ቦታዎች ላይ የከንፈር ላይ ሸክላ ያደረጉ ልጃገረዶች ዳንስ ልዩ ግርማ ሞገስ ያለው ነው። የዳንስ ምታቸው ከሸክላው ውዝዋዜ ጋር ተዋህዶ የሚፈጥረው ምስል በቀላሉ ከአይምሮ አይጠፋም) እና ጎረምሶች ሊያዩዋቸው በሚችሏቸው አጋጣሚዎች ላይ አድርገውት ሲወጡ ያገቡ ሴቶች ደግሞ ከብቶችን ሲያልቡ፣ ለባሎቻቸው ምግብ ሲያቀርቡ የእናትነት/የወይዘሮነት ግርማ ሞገስ እንዲያላብሳቸው ያደርጉታል። የከንፈር ላይ ሸክላ ያደረገች ሴት እንደ ህፃን አሊያም ሸክላውን እንዳላደረገች ‘አስቀያሚ’ ሴት አትንቀለቀልም። አረማመዷ ልክ ዜማ እንዳለው ሁሉ የተለካ፣ የረጋ እና ቀልብ የሚማርክ ነው። እቃ ለማንሳት ወይም ለአንዳች ነገር ማጎንበስ ወይ ደጎም ወደ አንድ አቅጣጫ ዞር ማለት ቢኖርባት እንኳን ፍፁም በተረጋጋ መንፈስ የሸክላውን ውዝዋዜ ከግምት በማስገባት ልዩ ምት እንዲፈጥር እና የተመልካቹን ቀልብ እንዲሰውር በማድረግ ነው።

ለአንዲት የሙርሲ ሴት የከንፈር ላይ ሸክላ ማድረግ ማለት በይፋ የማህበረሰቡ አካል መሆኗን ማረጋገጥ፣ ሙሉ ሰው መሆኗን ማሳየት ማለት ነው። ይህ የእድሜ ደረጃ እና ድርጊት የማንነቷን መገንቢያ ጡብ በፍቃዷ ማስቀመጥ የምትጀምርበት፣ በገላዋ እንደልቧ በማዘዝ የራሷ ገዢ፤ የራሷ ባለቤት እሷው መሆኗን የምታረጋግጥበት፣ በራስ መተማመኗን በማሳደግ ለመኖሯ ትርጉም የምትሰጥበት፣ በማነንቷ በመኩራት ከፈጣሪ የተሰጣትን ውበት እንካችሁ የምትልበት ከቅድመ አያቶቿ የወረሰችው ለልጅ ልጆቿ የምታወርሰው ልዩ ሀብቷ ነው።

93 views0 comments

Recent Posts

See All

Comments


bottom of page