top of page
Search
mastu89

የኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ማህበር/ ሀገር ፍቅር ቴአትር

ፋሽስት ኢጣሊያ በአፍሪካው ንጉስ እምዬ ምኒሊክ በ1888 ጥጋቡ በርዶለት፣ ተዋርዶ ከተመለሰ በኋላ አርባ አመታትን ሲያቄም፣ በጉልበት እና በሞራል ሲዘጋጅ ከርሞ ይህችን ፅጌረዳ የሆነች ሲያዩዋት ውበቷን መቋቋም የማይችሏት ሲቀርቧት ደግሞ እሾኋ የማያስጠጋ በአምላክ ቃልኪዳን የምትጠበቀውን ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን ዳግም ሊደፍር ምድሯን ረገጠ። አልደፈር ባይ የኢትዮጵያ ጀግኖችም አባቶቻቸው የማይሞከር የሚመስለውን ነጭን ማሸነፍን እውን አድርገው ለአፍሪካ ብሎም በመላው አለም ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ነፃነት የመጀመሪያውን የድል ብስራት ያሰሙበትን መንፈስ ተላብሰው በአየር በራሪ፣ በመርዝ ጋዝ፣ እና በተለያዩ ዘመን አመጣሽ የጦር መሳሪያ የታጀበውን ጠላት የጣሊያን ሰራዊትን ለመግጠም ከሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ተመሙ። በዚህ ግዜ ታዲያ በአዲስ አበባ የሚገኙ በሀገር ፍቅር የነደዱ ኢትዮጵያዊያን በተበታተነ አደረጃጀት አርባ አመት ሙሉ የታጠቀን ወራሪ ጠላት በቀላሉ ማሸነፍ እንደማይቻል ተረድተው ሀምሌ 11/1927 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዝብ የሀገር ፍቅር ማህበርን መሰረቱ። ማህበሩ ኢትዮጵያዊያን አባቶቻቸው በደም እና አጥንታቸው ጠብቀው ያስረከቧቸውን ዳር ድንበር እንዲያስጠብቁ፣ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው አንድነታቸውን ከምን ጊዜውም በላይ እንዲያጠናክሩ፣ በተለይ ደግሞ በመዲናይቱ አዲስ አበባ ያለው ህዝብ በአርበኝነት ስሜት ተነሳስቶ ለጦርነት እንዲዘጋጅ ማድረግን አላማው አድርጎ ተቋቋመ።

በዘመኑ የማስታወቂያ ሚኒስትር መኮንን ሀብተወልድ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ህዝቦች ሀገር ፍቅር ማህበር የመጀመሪያ መሰብሰቢያ ቦታው በወቅቱ የአራዳ አንደኛ ምድብ ችሎት የነበረ የራስ ሀይሉ ህንፃ እና በአካባቢው ያለ ትልቅ ዛፍ ስር አሊያም ሰፋ ያለ ሜዳ ላይ ነበር። ማህበሩ ህዝቡን ከሰበሰበ በኋላ በወቅቱ በነበሩ እንደ መኮንን ሀብተወልድ፣ ሀዲስ አለማየሁ፣ ወልደዮሀንስ ወልደጊዮርጊስ፣ እና ዮፍታሄ ንጉሴ ባሉ አንደበተ ርቱዕ ባለቅኔዎች የመድረክ ላይ ዲስኩር ይደረግ ነበር። የዲስኩሩ ማጠንጠኛ የሀገር ፍቅር፣ የነፃነት ክብር እንዲሁም የባርነት እና ቅኝ ግዛት ውርደት ነበር። ዲስኩሩ በየቀኑ ሲደጋግም ህዝቡም ቀስ በቀስ እየተሰላቸ ጉዳዩ አላማውን እየሳተ መምጣቱን የተመለከቱት ብልሁ የኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ማህበር፣ በኋላም የሀገር ፍቅር ቴአትር ስራስኪያጅ መኮንን ሀብተወልድ ለተሰብሳቢው ሁሉ ጠጅ እየገዙ ዲስኩራቸውን በአዝማሪ ጨዋታ እያዋዙ ማቅረብ ጀመሩ። ይህ ስልት ለተወሰነ ጊዜ ውጤታማ ቢያደርጋቸውም ማርም ሲበዛ ይመራልና ሰዉ በድጋሚ መሰላቸት ውስጥ ገባ። በዚህ ጊዜ ነበር መኮንን ሀብተወልድ ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን የህዝቡን ቀልብ በዘላቂነት ለመያዝ የሚያስችል ስልት የነደፉት። በዚህም የፈረንሳዩን የፍግ ቴአትር ቅርፅ “ኮሜዲያ ደላ አርቴ”ን በመጠቀም የተለያዩ ትርኢቶችን ማዘጋጀት ጀመሩ። “ኮሜዲያ ደላ አርቴ” በመሰረታዊነት ድንገቴ ፈጠራን የሚጠቀም የፍግ ተውኔት ዘርፍ ነው። ሚኒስትሩም ይህንኑ ግብዓት በመውሰድ ምንም አይነት የትውኔት ፅሁፍ በሌለበት እንደ ደራሲም እንደ አዘጋጅም በመሆን ተዋንያኑን “አንተ ይህንን በል” አንተ ደግሞ ይህንን በል” አንተ ይህንን ስትል እከሌ ደግሞ ይህንን ይበል” እያሉ በቃል የመጣላቸውን ሀሳብ እያስጠኑ ህዝቡን ማዝናናት እና ማነሳሳቱን ተያያዙት። መድረኩ የአቶ መኮንን ሀሳብ ማንፀባረቂያ እንጂ ቴአትር በቴአትርነቱ እራሱን ችሎ የሚቀርብበት መንገድ አልነበረም። የአቶ መኮንን ዋነኛ ሀሳብም ህዝቡን ማዝናናት ሳይሆን ረመጥ የሆነባቸውን የጣሊያንን ሀይል በተባበረ ክንድ ማስወገድ በመሆኑ ከሚቀርበው ትርኢት ይልቅ ዲስኩርና በሀገር ጉዳይ ላይ ያተኮረ ፕሮፓጋንዳ ይበዛው ነበር። ከትርኢቱ ጎን ለጎንም የጦር ሀሳባቸውን ለማሳካት የሚውል የገንዘብ መዋጮ ይሰበሰብ ነበር። የማህበሩ መነቃቃት በዚህ መልኩ እየቀጠለ ሄደና ትርኢት የማቅረቡ ነገር ህዝቡን የማያሰለች በመሆኑ በየሳምንቱ እሁድ እሁድ በቋሚነት መከወን ጀመረ።

የመድረክ ትርኢት ከመጀመሩ በፊት መሰንቆ ተጫዋቾች ከመድረኩ ጫፍ ላይ እየወጡ መዲናና ዘለሰኛን (መዲና እና ዘለሰኛ ለአምላክ ምስጋና የሚቀርብበት በቅኔ ግጥም የተሞላ መንፈሳዊ ዜማ ነው) ይጫወታሉ። ከዚያም መጋረጃው ይከፈትና የባህላዊ ሙዚቃ ትርኢት ይቀርባል። በመቀጠል የሙዚቃዊ ፍግ ቴአትር ባህሪ ያላቸው አጫጭር ተውኔቶች ይቀርባሉ። በመጨረሻም ረዥም ተውኔት ይቀርብና ሽብሸባ በተሞላበት ዝማሬ ይደመደማል።

ህዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ ሲቀሰቅስ እና አንድነተን ሲሰብክ የነበረው ማህበር በሚያዚያ ወር 1928፣ ከተቋቋመ ከዘጠኝ ወራት እጅግ ውጤታማ እንቅስቃሴ በኋላ በፋሽስት ጦር አዲስ አበባን መቆጣጠር ምክንያት ለመፍረስ ተገዷል። መስራቾቹ እና ዲስኩር አቅራቢዎቹም ግማሹ በውስጥ አርበኝነት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተሰማሩ፣ ግማሹ ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት በመሰደድ የአርበኝነት ስራውን አጧጧፈ። ከንጉሱ ጋር የተሻለ ቀረቤታ እና እድል ያላቸው ደግሞ ወደ አውሮፓ ተሰደዱ። የማህበሩም የመጀመሪያ ምዕራፍ በዚሁ ተደመደመ።

ከነፃነት በኋላ በግንቦት ወር 1934 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገር ፍቅር ማህበር በቀድሞ መስራቹ በአቶ መኮንን ሀብተወልድ በድጋሚ ተቋቋመ። በዚህ ግዜ ሲቋቋም እንደ ቀድሞው በማህበርነት ብቻ ሳይሆን እንደ ኪነ ጥበብ ቤትነትም ጭምር ነበር። መቀመጫውም ታዲያ በራስ ሀይሉ ህንፃ፣ በዛፍ ጥላ ስር ወይ ደግሞ ሜዳ ላይ ሳይሆን ህዝቡንና ስነ ጥበብን ባከበረ መልኩ በትክክለኛ አዳራሽ ውስጥ እንዲሆን አቶ መኮንን በእጅጉ ደክመዋል። በዚህም በጠላት ወረራ ግዜ የጣሊያን መኮንኖች ይዝናኑበት የነበረው በአሁኑ የሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ ግቢ ውስጥ የሚገኘው፣ ከ200 እስከ 300 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችለው “ኪው ክለብ” እንዲሰጠኝ ሲሉ ጥያቄያቸውን ለቀዳማዊ ኅይለስላሴ አቀረቡ። ጥያቄያቸው አዎንታዊ ምላሽ ካገኘ በኋላ እንደቀድሞው ዲስኩር የሚያቀርቡ ሳይሆን የዘፍን እና ጭፈራ ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች ከአብያተ ክርስቲያናት፣ ሆቴሎችና መሸታ ቤቶች ከባልደረባቸው በሻህ ተክለማሪያም (ከጠላት ወረራ በፊት ከአርመናዊው ኬቮርክ ናልባንዲያን ጋር በመሆን ሙዚቃ ያስተምሩ ነበር) ጋር በመሆን አሰባስበው ዝግጅቶቻቸውን ማቅረብ ቀጠሉ።

ጃንሆይ በ1947 ዓ.ም በአሜሪካ ጉብኝት ያደርጋሉ። ከጉብኝታቸው መልስም የአሜሪካ ቆይታቸውን የሚያሳይ መጠነ ሰፊ አውደ ርዕይ እንዲዘጋጅ ያዛሉ። ከዝግጅት መርሀ ግብሮቹ አንዱ ለአውደ ርዕዩ የሚመጥን ትልቅ አዳራሽ ማስገንባት ነበር። የአዳራሹ ግንባታ ሙሉ ሀላፊነት በኢትዮጵያ የቴአትር ቤት አዳራሾች ግንባታ ላይ አሻራቸው በጉልህ የተቀመጠው ጣሊያናዊው መሀንዲስ ቢያንካ ላይ ወደቀ። ቢያንካም በተለመደው ጥራት፣ ታማኝነት እና ፍፁም ታዛዥነት በተሰጠው ዲዛይን መሰረት ከፊት ለፊት መድረክ፣ ከኋላ ደግሞ ለንጉሳዊያኑ ቤተሰብ መቀመጫ የሚሆን ሰገነት ያለው ‘ግዙፍ’ አዳራሽ ሰርቶ አስረከበ። ከአውደ ርዕዩ በኋላ አዳራሹ ከቴአትር በስተቀር ለሌላ አገልግሎት መዋል የማይችል በመሆኑ ለኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ማህበር ሳምንታዊ ትርኢት አቅርቦት እንዲውል ተደረገ። ሀገር ፍቅር ቴአትርም የዛሬ አዳራሹን ለማግኘት በቃ። ይህ አዳራሽ አሁን ያለውን ቅርፅ የያዘው ግን በ1994 ዓ.ም አርቲስት ስዩም አያና ቴአትር ቤቱ ኪነ ጥበብን ብሎም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችን የሚያንፀባርቅ ይዘት ሊኖረው ይገባል ብሎ ባቀረበው ሀሳብ መሰረት የተሀድሶ ግንባታ ከተደረገለት በኋላ ነው።

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ማህበር/ ሀገር ፍቅር ቴአትር ከድል በኋላ እንደ አዲስ ሲቋቋም በቂ ሀብት ያልነበረው በመሆኑ ለሰራተኞቹ ደሞዝ እንዲሁም ለስራ ማስኬጃ የሚሆን ምንም አይነት ገቢ አልነበረውም። ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተደረገው ጥረትም በቅድሚያ በንጉሱ ትዕዛዝ ከመርካቶ ነጋዴዎች ለማህበሩ በሚል በሚሰበሰብ ገቢ እንዲተዳደር ተደረገ። በኋላም ቋሚ የገቢ ምንጭ አስፈላጊ በመሆኑ በእቴጌይቱ ድጋፍ በግቢው ውስጥ ከሚሰራ የስጋጃ ምንጣፍ ገቢ፣ ከጠንቋዮች ግብር (ጠንቋዮች ፈቃድ አውጥተው ግብር እየከፈሉ ይተዳደሩ ነበር። ግብሩም በቀጥታ ለሀገር ፍቅር ቴአትር ገቢ ይደረግ ነበር)፣ ከአዝማሪዎች የሚገኝ ቀረጥ፣ ከእስልምና ሀይማኖት የፅህፈት ቤት ኪራይ (በወቅቱ የእስልምና እምነት ማስተዳደሪያ ፅ/ቤት በሀገር ፍቅር ቴአትር ቅጥር ውስጥ ነበር)፣ ለተለያዩ በአላት ከሚደገስ ድግስ ከሚገኝ ገቢ፣ ከመፅሄት ሽያጭ (ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ መነን መፅሄት እና የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ በኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ማህበር ስር ነበር የሚታተሙት)፣ ከባካራ እና ሮሌት ቁማር ገቢ (ማህበሩ ቁማርን በህጋዊነት ያጫውት ነበር)፣ ከቀረጥ ድጎማ፣ ከሀረር የኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ማህበር ቅርንጫፍ፣ ከኦርኬስትራዎች፣ ከድርሰት ክፍያ፣ ከዝክረ ኪነጥበባት ቀረጥ፣ ኪው ክለብ ለመዝናናት ከሚገቡ ሰዎች የሚሰበሰብ የክራቫት ኪራይ (የምሽት ክለብ ገብቶ ለመዝናናት ክራቫት ማድረግ የግድ ነበር) የሚገኙ ገንዘቦች የቴአትር ቤቱ/ ማህበሩ ገቢ ማስገኛዎች ነበሩ።

የሀገር ፍቅር ማህበር ሀገር ፍቅር ቴአትር የሚለውን ስያሜ ያገኘው በታላቁ ባለቅኔ ፀጋዬ ገብረመድህን በ1961 ዓ.ም ነበር። ቴአትር ቤቱ ከአዲስ አበባ የጥበብ አቅርቦቶቹ በተጨማሪ ተጓዥ የቴአትር ቡድን በማቋቋም በፈረስ እና በቅሎ በየክፍላተ ሀገራቱ በመዘዋወር የቴአትር ትርኢት ያቀርብ ነበር። በዚህም የቴአትር ጥበብን ተደራሽነት በከፍተኛ ሁኔታ ከማሳደጉም በላይ ለተቋሙ ተጨማሪ ገቢ ማስገኘትም ችሏል።

ሀገር ፍቅር ቴአትር ለዘመናዊ ተውኔት አፃፃፍና ዝግጅት ጥርጊያ ጎዳና መክፈት ከጀመረበት ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ በኢፍትሀዊነት፣ በምዕራባዊያን ባህል ወረራ፣ እና ማህበራዊ ቀውሶች ላይ የህብረተሰቡን አስተሳሰብ በእርግጥም የቀየሩ በርካታ የጥበብ ስራዎችን አቅርቧል። በቴአትር ቤቱ ውስጥ ከምናገኛቸው ታላላቅ የጥበብ ፈርጦች መካከል ተስፋዬ አበበ፣ አበራ ደስታ፣ ዘነበች ታደሰ፣ የሺ ተክለወልድ፣ ሙናዬ መንበሩ፣ በላይነሽ አመዴ፣ በቀለ ወልደፃዲቅ፣ እና ግርማ ብስራት በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው።

በሀገር ፍቅር ቴአትር በተለይም ከ1940 ዓ.ም እስከ 1960 ዓ.ም ይቀርቡ የነበሩ ስራዎች በአብዛኛው መልካም ስነምግባርን ለማስተማር ገፀ ባህሪያቱ በመልአክ እና ሰይጣን ተምሳሌትነት የተፃፉ ነገር ግን ቴክኒካዊ የአቀራርብ ጉድለት የነበረባቸው ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪ የመድረክ ግንባታ አቅማቸው እጅግ ደካማ የነበረ በመሆኑ ለአንድ ቴአትር የተገነባ መድረክ ለሌላ ተውኔትም ያገለግል ነበር።

ሀገር ፍቅር ቴአትር ሲነሳ ከላይ ከተጠቀሱት የጥበብ ፈርጦች በተጨማሪ በሁለገብ ከያኒነታቸው እስካለንበት ዘመን ድረስ መተኪያ ያልተገኘላቸው፣ ለሀገር ፍቅር ቴአትር ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ቴአትር እድገት ምሶሶ የሆኑ ሶስት ባለሞያዎችን ማንሳት የግድ ነው፡ ኢዮኤል ዮሀንስ፣ ማቲዎስ በቀለ እና መላኩ አሻግሬ። ስለ እነዚህ ከያኒያን ስራዎች በቀጣይ ምጥን ፅሁፌ እመለሳለሁ ለዛሬ ግን በዚሁ ልሰናበት። ቸር ይግጠመን።





85 views0 comments

Comments


bottom of page