top of page
Search
mastu89

የእውቀት ሽግግር በቴአትር ቤቶቻችን

የደቡብ ኦሞ ቴአትር ኩባንያ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የቴአትር ጥበብ እስካሁን በስፋት ባልታየ መነፅር ለመመልከት እና የሀገራችን ጠበብት እየባዘኑበት ያለውን የኢትዮጵያን የቴአትር ቅርፅ የማግኘት ጥረት በተቻለው አቅም ለመደገፍ ቆርጦ ተነስቷል።

ኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሰራቸው የቴአትር ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የአቅም ማጎልበት ስልጠናዎች ሌላው የትኩረት አቅጣጫዎቹ ናቸው። በዚህም በሰሜን አሜሪካ ኦሃዮ ግዛት ከሚገኘው ሴንሴናቲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በመድረክ ላይ ብርሀን ስርጭት ዲዛይን አንቱ ከተባሉ እና በመላው አለም እየተዘዋወሩ ታላላቅ የሙዚቃ ድግሶችን፣ የቴአትር እና ዳንስ እንዲሁም የኦፔራ ዝግጆትችን፣ የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን በአለ ሲመት ጨምሮ የተለያዩ ታላላቅ ሁነቶችን የመብራት ስርጭት እንከን የለሽ ካደረጉ ባለሙያዎቹ መካከል አንዷ የሆኑትን ፕሮፌሰር ሻሮን ሁዚንጋን (https://www.dutchdameproductions.uk/) በማስመጣት በመጀመሪያ በመዲናችን ከሚገኙ ሁሉም ቴአትር ቤቶች ለተውጣጡ የብርሀን ስርጭት ባለሞያዎች የሁለት ቀን መሰረታዊ ስልጠና ሰጥቷል።

ስልጠናው እጅግ የተሰካ የነበረ ሲሆን የብሄራዊ ቴአትር ስራ አስኪያጅ አቶ ማንያዘዋል እንደሻው ለስልጠናው ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ሁሉንም ቴአትር ቤቶች በማስተባበር እና እጅግ ምቹ የሆነ የስልጠና ቦታ በማመቻቸት ከኩባንያችን እቅድ እጅግ በላቀ መልኩ የተሳካ ቆይታ እንዲኖረን አድርገዋል። ምስጋናችንን እነሆ!

ሰልጣኝ የብርሀን ስርጭት ባለሞያዎችም በሚያበረታታ ተሳትፎ እና በግልፅ በሚታይ የእውቀት እና ቴክኖሎጂ ጥማት ሁለቷን ቀን ልክ እንደ ሁለት ደቂቃ ፉት አድርገዋት ለተጨማሪ እውቀት ሲጓጉ ተመልክተናል። እንዲህ አይነት ተግባር ቀመስ ስልጠናዎች እጥረት ያሰቃያቸው የድምፅ ግብአት ስርጭት ባለሞያዎች እና ጥቂት የቴአትር አዘጋጆችም የስልጠናው አካል መሆን ኩባንያችን አቅዶበት የተነሳው የእውቀት ሽግግር ፕሮግራም ትክክለኛ እና ወቅታዊ መሆኑን አረጋግጦልናል። በቀጣይም በሌሎች መስኮች በእውቀት ሽግግር እና በግብአት አቅርቦት የተቻለንን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እየገባን መሰል ስልጠናዎችን እና ድጋፎችን የማድረግ ፍላጎት እና አቅም ያላችሁ በሙሉ ነቃ ነቃ እንድትሉ አደራ እያልን በዚሁ እንሰናበት። በቀጣዩ ፅሁፍ ተመሳሳይ ስልጠና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አድርገን የነበረውን ግብረመልስ እና ሁኔታ እናስቃኛችኋለን። ቸር ይግጠመን።







31 views0 comments

Comments


bottom of page