top of page
Search
  • mastu89

ባለሪኮርዱ ሁለገብ ከያኒ

Updated: Mar 22, 2022

“አፈጣጠሩም አሟሟቱም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ነበር” የተባለለት ይህ ከ100 አመታት የኢትዮጵያ ዘመናዊ የቴአትር ታሪክ ውስጥ እርሱ የቴአትር ጥበብ ሞያን ከተቀላቀለ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለ79 አመታት በማንም ያልተሰበረ ሪኮርድ ያለው ሁለገብ ከያኒ እንደ አንዳንዶቹ በ1922 ዓ.ም እንደ ሌሎች አጥኚዎች ደግሞ በ1927 ዓ.ም (የሀገራችን በተለይም የቴአትር ጥበብ ሙያተኞች እና አጥኚዎች ችግር በማስረጃ የተደገፈ፣ እንደፀሀፊው ብርታት እና ድክመት ሳይሆን እንደ እውነታው የተፃፈ የታሪክ ሰነድ እጦት መሆኑን ልብ ይሏል) በመንፈሳዊ ህይወታቸው እጅግ ጠንካራ ከሚባሉት አባታቸው አቶ ዮሀንስ ትርፌ እና እናታቸው ወይዘሮ አየለች ደምሴ በመዲናችን አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ካዛንቺስ ተብሎ በሚታወቀው ባለ ብዙ ገፆች መንደር ተወለደ። ‘የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል’ እንዲሉ አበው የዚህ ታላቅ የኪነጥበብ ሰው ጉዞ የሰመረ እንደሚሆን በቅኔ እና በሀይማኖት ትምህርት (በወቅቱ ሀይማኖታዊ፣ ተፈጥሮአዊ እና ሳይንሳዊ እውቀቶች በተለያየ ደረጃ በዋነኛነት የሚሰራጩት በሀይማኖት ትምህርቶች ውስጥ ነበር) ከዘለቁት አባቱ መረዳት ይቻላል። የዚህች ምጥን ዋና ማጠንጠኛ የሆነውን አምራች ፀሀፌ ተውኔት የውልደት አመት በዛሬው ፅሁፋችን ውስጥ “1927 ዓ.ም ነው” የሚለውን የምንወስድ ይሆናል። ምክንያቱም በኋላ ላይ በምናነሳው የከያኒው የግል ንግግር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቴአትር ስራ የተጠራው በ1935 ዓ.ም በስምንት አመቱ እንደሆነ ይናገራል። ቀላሉን ሂሳብ እናንተው ስሩት።

ይህ ተዋናይ፣ አዘጋጅ፣ ድምፃዊ፣ ተወዛዋዥ፣ አወዛዋዥ፣ ገጣሚ፣ ዜማ አውጪ፣ አሰልጣኝ፣ ፀሀፌ ተውኔት፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች (የትኛውን መሳሪያ ይጫወት እንደነበር ግን ማግኘት አልቻልኩም። የምታውቁ በአስተያየት መስጫው ውስጥ አሳውቁን)፣ የቴአትር ቤት አስተዳዳሪ ባለሪኮርዱ ሁለገብ ከያኒ ኢዮዔል ዮሀንስ ይባላል። ኢዮኤል የእውቀት መንገዱን ‘ሀ’ ብሎ የጀመረው ሊቀ ጠበብት ሀይለጊዮርጊስ አባይ የተባሉ መምህር ጋር ፊደል በመቁጠር እና ዳዊት በመድገም ነበር። በወቅቱ የቤተክህነት እውቀት ከሚታፈስባቸው በሰሜን ሸዋ እና ጎጃም ካሉ ገዳማት በመዘዋወርም (ምንም እንኳ ወደ ገዳማቱ የሄደበት መንገድ በፍላጎቱ ላይ የተመሰረተ ባይሆንም) ገና በልጅነቱ የተጠማውን እውቀት እስኪበቃው ድረስ ቀስሟል።

ፋሺስቱ የጣሊያን ወራሪ በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን አርበኞች በማያዳግም መልኩ አከርካሪውን ከተመታ እና ወደመጣበት አፍሮ ከተመለሰ በኋላ በ1934 ዓ.ም የቀድሞው የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ መኮንን ሀብተወልድ የሀገር ፍቅር ማህበርንን በድጋሚ አቋቋሙ። በቀደመው ስለ ሀገር ፍቅር ባጋራኋችሁ ምጥን ፅሁፍ ላይ (https://www.southomotheatre.com/post/%E1%8B%A8%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%88%80%E1%8C%88%E1%88%AD-%E1%8D%8D%E1%89%85%E1%88%AD-%E1%88%9B%E1%88%85%E1%89%A0%E1%88%AD--%E1%88%80%E1%8C%88%E1%88%AD-%E1%8D%8D%E1%89%85%E1%88%AD-%E1%89%B4%E1%8A%A0%E1%89%B5%E1%88%AD) አቶ መኮንን ቴአትር ቤቱን በተደራጀ መልኩ ለማቋቋም የአዳራሽ ጥያቄ አቅርበው ሲያበቁ ተዋንያንን፣ ዘፋኞችንና ተወዛዋዦችን ከየአብያተ ክርስቲያናቱ እና መሸታ ቤቶቹ ይሰበስቡ እንደነበር አንብበናል። ኢዮዔልም በዚሁ የሀገር ፍቅር ቴአትር አቅኚ ከተገኙ የድንቅ ተሰጥኦ ባለቤቶች አንዱ ነበር። ሁለገብ ከያኒው እንዴት ከሚኒስትር መኮንን ሀብተወልድ ጋር እንደተገናኘ እና የቴአትር ሞያን ሲጀምር የገጠመውን የማይቻል የሚመስል መሰናክል እንዲህ ሲል በአንደበቱ አስረድቷል፡

ከዕለታት አንድ ቀን በአዲስ አበባ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ በዲያቆንነት ሞያ ላይ ሳለሁ ክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ ድምፄን ሰምተው በማስጠራት በሀገር ፍቅር ማህበር እንድሰራና በእርሳቸውም ቤት እንድኖር አደረጉኝ። ጊዜውም 1935 ዓ.ም ሲሆን እድሜዬ ስምንት አመት ነበር። ወዲያውም ድምፄ በራዲዮ እንደተሰማ ወላጆቼ ሰምተው በመናደድ በፖሊስ አሳድደው ያዙኝና ለቅኔ ትምህርት ወደ ጎጃም ላኩኝ። በዚያም ሁለት አመት ያክል እንደተማርኩ ክቡር አቶ መኮንን ዳግም በፊናንስ ዘበኞች አሳድነው አስመጡኝና ስራዬን እንድጀምር አስደረጉኝ። ወላጆቼም እንዳይቀየሙኝ አጥጋቢ ምክር ሰጥተው ስላስታረቁኝ ልቤ ረግቶ መጫወቱን ቀጠልኩ።

የሌላው የኢትዮጵያ ቴአትር አይን - ማቴዎስ በቀለ ደቀመዝሙር የሆነው ኢዮዔል የመድረክ ህይወቱን አሃዱ ያለው በ1942 (?) “የወይን ባለቤት” በተሰኘው ቴአትር ነበር። በቀጣዩ አመትም “ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን” በተባለ ተውኔት ላይ እንደ አንድ መስሪያ ቤት ፀሀፊ ሆኖ ተጫውቷል። ይህ ቴአትር ከአዲስ አበባ ውጪ በወሎ፣ ከፋ፣ ወለጋ፣ ኢሉባቦር፣ ሀረርጌ፣ ሲዳሞ እና ኤርትራ ክፍላተ ሀገራት ታይቷል (ቴአትር በዛ ዘመን ኢትዮጵያን ሲያዳርስ፣ በጥበብ አንድ ሲያደርግ መንገድ፣ ገንዘብ፣ የተሻሻሉ አዳራሾች ወዘተ አልመኖራቸውን ልብ ይሉና ዘመንዎን እንዲቃኙ ተጋብዘዋል)። በዜማ ደግሞ የኢዮዔል የመጀመሪያ ዜማ ‘ነፃነት ገዳሜ’ የተባለችው ናት። ስለ ዜማ እና ቴአትር ስራዎቹ ኢዮዔል እንዲህ ይላል፡

‘ነፃነት ገዳሜ’ን ተጫወትኋት እንጂ የደረሷት ታላቁ ሊቅ ቀኝጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ናቸው። እስከዛሬ ድረስ ከሶስት መቶ በላይ ዜማዎች፣ ሰላሳ አምስት ቴአትሮችና ሰላሳ አምስት የሚደርሱ ኮሜዲዎች (ኮሜዲዎቹ እንደ ቴአትር በስነስርአት የሚፃፉ ባለመሆኑ እና በመነሻ ሀሳብ ላይ ብቻ ተመስርተው በብዛት በድንገቴ ፈጠራ የሚተወኑ በመሆኑ እንደ ሙሉ ቴአትር አይቆጥራቸውም) በመድረስ ለህዝብ እንዲደርሱ አድርጌያለሁ። ከዜማዎቹም መካከል “ያገር ፍቅር ትዝታው” የተባለውን አብልጬ እወዳለሁ።

ኢዮዔል ለጥበብ ሞያ ከሚቆረቆሩ ታጋዮች መካከል ነበር። ሙዚቃ ሞያን ያለችሎታቸው ገብተው ስለሚያቦኩ እና በነቀዘ አስተያየታቸው ስለሚያንኳስሱ ሰዎች የግል ህይወቱን ዋቢ በማድረግ ይህንን ብሎ ነበር፡

ብዙዎች ሰዎች ዘፋኝን ወይም ሙዚቀኛነትን እንደቀላል ነገር ቆጥረው ሲመለከቱት በማየቴ አዝናለሁ። በዚህም የተነሳ በጋብቻ በኩል ችግር እንደገጠመኝ ልደብቅ አልሻም፤ ሆኖም ባሁኑ ወቅት ሙዚቃን እየወደዱ አስደሳቾቻቸውን የሚያቃልሉት ተሻሽለዋል። ወደፊትም ሁሉም በየሙያው ድካም እንዳለበት በመረዳት አጉሉን ፈሊጥ ፈፅመው ያወድሙታል የማለት እምነት አለኝ።

ተወዳዳሪ በሌለው መልኩ ከ100 በላይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የኢዮዔል ቴአትሮች በደምሳሳው በሶስት ዋና ዋና መደቦች ሊከፈሉ ይችላሉ። ረዣዥም፣ አጫጭር እና ሙዚቃዊ በመባል። ቴአትሮቹ በእነዚህ ሶስት ሰፋፊ መደቦች ይከፈሉ እንጂ ሀይማኖታዊ፣ ስነምግባራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ፣ ማህበራዊ ወዘተ ይዘት ያላቸው እያልንም ልንከፍላቸው እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ኢዮዔል የመጀመሪያው የሙዚቃዊ ቴአትር ፀሀፊና አዘጋጅ እንደመሆኑ ከቴአትሮቹ ከፊሉ ሙዚቃዊ ቴአትር ነው ልንልም እንችላለን። ነገር ግን ሁሉን በየቅርፁ እና ይዘቱ ለመተንተን የዚህች ምጥን ባህሪ አይፈቅድምና በሶስቱ ቅርፆች መድበን መዘርዝሩን ብቻ እንመልከት። ጠለቅ ያለ ተውኔታዊ ትንታኔው በሌላ ፅሁፍ ወይም አጥኚ ሊቀርብ ይችላል።

ከኢዮዔል ዮሀንስ ረዣዥም ተውኔቶች መካከል የተወሰኑት፡ “አቻ ጋብቻ”፣ “የህይወት ፋና የወጣት ዜና”፣ “ቃልኪዳን አፍራሹ”፣ “ዘጠኝ ፈተና ያለፈ ጀግና”፣ “የእግዚአብሄር ቸርነት የአርበኞች ጀግንነት”፣ “ስራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው”፣ “ልደት”፣ “ምን ትችል ምድር”፣ “ከእጅ አይሻል ዶማ”፣ “የአምላክ ህሊና የሰው ልቦና”፣ “የሰው ሆዱ የወፍ ወንዱ”፣ “መልካዓ ምድር”፣ “ወርቅ ላበደረ ጠጠር”፣ “ነፃነት ታደሰ”፣ “መንገደ ሰማይ” ናቸው። ከእነዚህ ረዣዥም ተውኔቶች መካከል ኢዮዔልን የምንጊዜም ሪኮርድ ባለቤት እንዲሆን ያስቻለውን ቴአትር ብቻ በወፍ በረር እንመልከት።

“ዘጠኝ ፈተና ያለፈ ጀግና” የተሰኘው ረዥም ቴአትር በአስር ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን ዘጠኙ ምዕራፎች ዘጠኝ የተለያዩ የስካር አይነቶችን ያሳያሉ። ሁላችንም እንደምናውቀው አንዳንድ ስካር ያስቃል፣ ያስኮርፋል፣ ያደባድባል፣ ሌላው ደግሞ ያስለቅሳል። ሀንጎቨርና መዘዙም እንደየአይነቱ ይለያያል። ይህ ቴአትር ታዲያ ምንም እንኳን የየምዕራፉ ጭብጥ መጠጥ እና ስካር ቢሆንም እያንዳንዱ ክፍል በራሱ ምሉዕ የሆነ ጅማሬ፣ መሀል እና መጨረሻ ያለው ነው። “ዘጠኝ ፈተና ያለፈ ጀግና” በዘጠኙ ክፍሎቹ ያነሳቸው ጥያቄዎች እና የፈጠራቸው ጡዘቶች በአስረኛው ምዕራፍ መልስ እና ልቀታቸውን ያገኛሉ። የየምዕራፉ አቀንቃኝ ገፀባህሪያት በመጨረሻው ክፍል ላይ ይገናኛሉ። የሀገር ፍቅር ልዩ መፅሄት በ1991 ዓ.ም እትሙ ስለዚህ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ በረዥም ተውኔትነት ተወዳዳሪ ሳላልተገኘለት ቴአትር የሚከተለውን አስነብቧል፡

... “ዘጠኝ ፈተና ያለፈ ጀግና” የተሰኘው ተውኔት ለህዝብ ታይቶ ያለቀው በአስር ተከታታይ ሳምንታት ሲሆን በየሳምንቱ ለማየት የሚመጣውን ተመልካች በ’ይቀጥላል’ ያሰናብቱት ነበር። ... የሚያስገርመን ይህ ብቻም አይደለም የታሪኩ ሰዎች (ገፀባህሪያት) መብዛትም ሌላው ታምር የሚያሰኝ ነው። በድግግሞሽ በየምዕራፉ ከሚታዩት ሌላ ሀምሳ ሁለት ገፀባህሪያት ይገኙበታል። ሆኖም ግን እያንዳንዱ ምዕራፍ በሳምንት አንድ ጊዜ እሁድ ስለሚቀርብ ሳምንት በቀረበው ምዕራፍ የተሳተፉ ተዋንያን በሚቀጥለው ሳምንት ተከታዩን ምዕራፍ አዋጥተው እንዲቀርቡ ይደረግ ነበር። (አንድ ተዋናይ ተደራቢ ገፀባህሪያትን ይጫወት ነበር ማለት ነው)። ...

ይህ በዝርው የተፃፈው የሀገራችን ረዥሙ ቴአትር ሀያ ሶስት ተዋንያንን ያሳተፈ ሲሆን እነሱም፡ ለገሰ በላቸው፣ አበራ ደስታ፣ አሰለፈች አሽኔ፣ ዘነበች ታደሰ፣ ውብሸት ወርቅአለማሁ፣ አዳነች ተሰማ፣ በላይነሽ አመዴ፣ ሳህሉ እዝነህ፣ ጥላሁን ወ/ማሪያም፣ በቀለ ወ/ፃዲቅ፣ ሳህሉ ሸንቁጤ፣ ንጉሴ ሀይሉ፣ ወርቅአገኘሁ ምስጋናው፣ መዝሙር ገ/ወልድ፣ ክፍሉ ሀይሌ፣ በጋሻው ተ/ማሪያም፣ የሺ ተ/ወልድ፣ ኢዮዔል ዮሀንስ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ግርማ ብስራት፣ ፍሬው ሀይሉ፣ በላይነሽ ውባንተ፣ እና ታደሰ ለማ ናቸው።

ወደ ሁለተኛው የሁለገብ ከያኒ ኢዮዔል ዮሀንስ የቴአትር አይነቶች ስንመጣ አጫጭር ድራማዎቹን እናገኛለን። ባለ ሪኮርዱ የሀገር ፍቅር ፍሬ ከፃፋቸውና ካዘጋጃቸው አጫጭር ተውኔቶች መካከል፡ “የልጃገረድ ሳሎን”፣ “ሳይቸግር ጤፍ ብድር”፣ “የሰው ክብሩ ግብሩ”፣ “ዞሮ ዞሮ ሁሉም ዜሮ”፣ “የህይወት መራራ”፣ “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች”፣ “አመድ በዱቄት ይስቃል”፣ “የዘመኑ ነቢይ”፣ “ቀዩ ለሊት”፣ “ካሜራ”፣ “በሬ ካራጁ”፣ “ውጦ ቁልጭ”፣ “የቀበሮ ባህታዊ”፣ “አድር ባይ”፣ “አዳም”፣ “መንገደኛው አዝማሪ”፣ “የሰላም ልዑካን”፣ እና “በህግ አምላክ” የሚሉት ይገኙበታል። እነዚህ አጫጭር ተውኔቶች እራሳቸውን ችለው በሙሉ ዝግጅት ይቀርቡ የነበሩ ሳይሆን በተለያዩ ፕሮግራሞች እና ሙዚቃዎች መሀል፣ ከዚያም በሬዲዮና ቴሌቪዥን ይተላለፉ የነበሩ ናቸው።

በሶስተኛ ደረጃ የከፈልናቸው የከያኒው የተመዘገቡ ሙዚቃዊ ቴአትሮች መዘርዝር፡ “ሀይማኖት መሰረት መተባበር ጉልበት”፣ “ጊዜ ወርቅ”፣ “አስራ ሁለት ጠቅላይ ግዛት”፣ “የአባቶች ሙያ የጦር ገበያ”፣ “ብቸኛ የሀሳብ ጓደኛ”፣ “ሰው ከጠራው እህል ውሀ የመራው”፣ “ጎልማሳው መንገደኛ ለፍቅር የማይተኛ”፣ “ያገሬ ተራራ”፣ “የውሀ ሚስጥር”፣ “አዲስ ፍቅር ያመናቅር”፣ “የሴት ፍርሀቷ እስከ መቀነቷ”፣ “የሀገር ፍቅር ትዝታው”፣ “ማንጠግቦሽ”፣ “ይመሻል ይነጋል”፣ “ዓለም ነጋዴ ነች”፣ “ደጉ ሰው”፣ “ወንድሜ ተነስ ወፎቹ ተንጫጩ”፣ “የደጄ አበባ”፣ “በሀብትሽ እወቂ”፣ “ኦኤዩ”፣ “ሀገር መውደድ”፣ “ዶሮ ማታ”፣ እና “ከልደት እስከ ሞት” ናቸው። ሙዚቃዊ ተውኔቶቹ በሀይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው። ኢዮዔል ከሀያ በላይ ሙዚቃዊ ተውኔቶችን በመፃፍ እና በማዘጋጀትም የኢትዮጵያን የሙዚቃዊ ቴአትር ሪኮርድ የያዘ ባለሞያ ነው። የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር አንድ መቶ አመታትን ሲያስቆጥር የኢዮዔልን ሪኮርዶች የሚጋራ ወይ የሚያሻሽል ሳይሆን አጠገቡ እንኳን ለመድረስ የሞከረ አንድም ከያኒ አልተገኘም (ጎበዝ እንበርታ እንጂ)

ኢዮዔል ቴአትሮችን እንዲህ በገፍ ይፃፍና ያዘጋጅ እንጂ ቴአትሮቹ ከጉድለት የፀዱ አልነበሩም። በተለይ የሙዚቃዊ ተውኔቶቹ ጭብጥ ከሙዚቃዎቹ እና ውዝዋዜዎቹ ጋር የተዋሃዱ እና አንድ አይነት መልዕክት ያዘሉ አልነበሩም። ሁለቱም የማይገናኙ ነገር ግን ቴአትሩን የሚያዝናና ለማድረግ እንደ እረፍት መስጫነት የሚያገለግሉ ሙዚቃዎች የነበሩባቸው አቅርቦቶች ነበሩ ለማለት እንችላለን። ከኢዮዔል ሪኮርዶች መካከል ሌላው የፃፋቸውን ተውኔቶች እራሱ በማዘጋጀት ወደር የማይገኝለት መሆኑ ነው። በአንድ ቴአትር ቤት ብቻ በመወሰን እጅግ ብዙ ተውኔቶችን ማቅረብ ሌላ ተገዳዳሪ ያላገኘለት ሪኮርዱ ነው። “ልደት” ከተሰኘው ቴአትር በስተቀር ሁሉንም ቴአትሮቹን በሀገር ፍቅር ቴአትር ብቻ ነው ያቀረበው። “ልደት” ቴአትር ስለ ጃንሆይ የተፃፈ በመሆኑ ለአንድ ጊዜ ብቻ በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ቴአትር (ብሄራዊ ቴአትር) እንዲታይ ተደርጓል።

የቴአትር ትምህርት ባልተስፋፋበት፣ ጥበቡ በተለያዩ የጥናት እና ምርምር ውጤቶች ባልተራቀቀበት፣ ህዝባችንም ለጥበቡ ይህ ነው የሚባል ቁብ በማይሰጥበት ዘመን የግል ተሰጥኦውን እና ከታላላቆቹ ያገኘውን መጠነኛ ስልጠና ብቻ በመጠቀም ሽቅርቅሩ ኢዮኤል ዮሀንስ ለ79 አመታት የዘለቁ ሪኮርዶች መያዝ ችሏል። ዛሬስ? የያኔውን ዘመን ሁሉን አቀፍ የጥበብ መከራ ካሁን ዘመን መደላድሎች ጋር አላነፃፅርም፣ ጥያቄዬንም አላብራራም ምክንያቱም ለሁላችንም ግልፅ ነውና። የቤት ስራውን ለግል፣ ለቡድን፣ እና ለየተቋሙ በመስጠት ልሰናበት! ቸር ይግጠመን።


Eyoel Yohannes

62 views0 comments
bottom of page