top of page
Search
  • mastu89

ተጓዡ የኢትዮጵያ ቴአትር አምድ

የምጥኔ አንባቢዎች እንደምን ከርማችሁልኛል? ዛሬ ትውልዱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሆኖ ለሙሉ ኢትዮጵያ የጥበብ ብርሀንን ስለፈነጠቀ ድንቅ ኢትዮጵያዊ አወጋችኋለሁ። በቀድሞው ሸዋ ክፍለ ሀገር ተጉለት እና ቡልጋ አውራጃ በ1925 ዓ.ም የኢትዮጵያን ቴአትር ከአንድ ምዕራፍ ወደ ቀጣዩ ያሸጋገረው ሁለገብ ከያኒ መላኩ አሻግሬ ይህችን የመከራ አለም ተቀላቀለ። ስለ ድምፃዊ፣ አዘጋጅ፣ ተዋናይ፣ ፀሀፌ ተውኔት፣ የዘፈን ግጥም እና ዜማ ደራሲ መላኩ አሻግሬ የትውልድ ዘመን የተለያየ ሀሳብ የሚያነሱ ፅሁፎችን ተመልክቻለሁ እኔ ግን 1925 የሚለውን እወስዳለሁ ምክንያቱም ሁሉም ፅሁፎች መላኩ በ1942 ዓ.ም በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ትምህርቱን ሲከታተል እድሜው 17 እንደነበር ይስማማሉ። ሂሳቡን አግዙኝ እንግዲያው።

መላኩ እስከ አምስት አመቱ ድረስ በእናት እና አባቱ እቅፍ ውስጥ በሞቀ ቤት ሲቦርቅ ከኖረ በኋላ በ1930 አባቱ ከዚህ አለም ድካም ሲያርፉ የኑሮዋቸው መዘውርም ቀድሞ ያልገመቱትን አቅጣጫ ያዘ። ምንም ነገር ያለምክንያት አይሆንምና የመላኩ አባት እረፍት ያስከተለው የህይወት ለውጥ ለብዙ ኢትዮጵያዊያን የብርሀን መንገድን ፈጥሯል። ባላቸውን በሞት ያጡት ወይዘሮ ወርቅነሽ ልጃቸውን ማሳደጊያ መንገድ ለመፈለግ ወደ አዲስ አበባ ፈልሰው በተለምዶ ቀጨኔ መድሀኔአለም የሚባለው ሰፈር ከተሙ። ለጥበብ የተመረጠው መላኩም የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ የሆነውን እግዚአብሄርን መፍራት ሊማር ቀጨኔ መድሀኔአለም ተመዘገበ። መንፈሳዊ ትምህርቱን በቀጨኔ መድሀኔአለም ጀምሮ ቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አጠናቋል። በመንፈሳዊ ህይወቱ ጉድፍ የማይወጣለት ይህ ብላቴና እጅግ ለየት ያለ የዜማ ችሎታ ነበረው። ይህ ችሎታውም ህይወቱ እስካለፈችበት ሰኔ 1/1985 ዓ.ም ድረስ ታምኖ ለኖረለት ሙያው መንገድ ጠርጎለታል።

በሺህ ዘጠኝ መቶ አርባ ሁለት ዓ.ም ብላቴናው መላኩ በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳለ አቶ በትሩ ወልደዮሀንስ የተባሉ የማዘጋጃ ቤት ሰራተኛ ቴአትር ቤታቸው ለሚያዘጋጀው የሰነ ስቅለት ቴአትር ድምፀ መረዋ ዘማሪ ለመመልመል ወደ ቅድስት ስላሴ ያመራሉ። በዚህ ግዜ ነበር መላኩ ከመክሊቱ ጋር የተገናኘው። መላኩ በዚሁ “ስነ ስቅለት” በተሰኘው ቴአትር ውስጥ በዘማሪነት በመሳተፍ የቴአትር ጥበብ ህይወቱን ሀ ብሎ ጀመረ። ቴአትሩ ከመድረክ ሲወርድ ታዲያ መላኩ ወደ መንፈሳዊ ኮሌጁ በመመለስ ፈንታ በማዘጋጃ ቴአትር ቤት በከበሮ መቺነት እና በዘፋኝነት ተቀጥሮ ለተወሰኑ ወራት አገልግሏል።

መላኩ አሻግሬ በተውኔት ስራ ላይ በቀጥታ መሳተፍ የጀመረው በሁለገብ ከያኒ ማቴዎስ በቀለ (https://www.southomotheatre.com/post/%E1%88%80%E1%8C%88%E1%88%AD-%E1%8A%A0%E1%8D%8D%E1%89%83%E1%88%AA%E1%8B%8D-%E1%88%9B%E1%89%B4%E1%8B%8E%E1%88%B5-%E1%89%A0%E1%89%80%E1%88%88) መሪነት በሀገር ፍቅር ማህበር በተዋናይነት እና በዘፋኝነት ከተቀጠረ በኋላ ነው። የመላኩ የሀገር ፍቅር ማህበር ቆይታ የኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ማነቆ በሆነው የመረጃዎች መዛባት የተነሳ አሻሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የቴአትር ታሪካችን በግለሰቦች አንደበት እንደየግል አተያያቸው እና የማስታወስ ብቃታቸው የጠበበ በመሆኑ ተጨባጭ ማስረጃ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው። መላኩም የዚሁ የተዛባ ታሪክ ሰለባ ነው። ለዚህች ምጥን ያጣቀስኳቸው ፅሁፎችም በሀገር ፍቅር ማህበር ቆይታው ላይ የተለያየ ሃሳብ ይዘዋል። የተወሰኑት በሀገር ፍቅር ማህበር ቴአትር የሀረር ቅርንጫፍ ተመድቦ ሰርቷል ሲሉ ገሚሱ ደግሞ የለም ከማቲዎስ በቀለ “አንድነት የቴአትር ቡድን” ጋር በመሆን ነው ወደ ሀረር ያቀናው ይላሉ። የሆነው ሆኖ ለዚህ ፅሁፍ መላኩ ወደ ሀረር ክፍለ ሀገር ሄዶ ቴአትር ማሳየቱን መያዝ በቂ ነው።

መላኩ ከሀገር ፍቅር ማህበር በፈቃዱ ከለቀቀ በኋላ የማቴዎስ በቀለን አንድነት የቴአትር ቡድን ተቀላቅሏል። ከቡድኑ ጋር በመሆንም በርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎችን በመዘዋወር የቴአትር ጨዋታዎችን አቅርቧል። ከአንድነት የቴአትር ቡድን ከለቀቀ በኋላም በድጋሚ ወደ ሀገር ፍቅር ተመልሶ ካገለገለ በኋላ በ1949 ዓ.ም የክቡር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል ቅጥር ሆነ። መላኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ፅፎ ለመድረክ ያበቃው ተውኔት በአንዳንዶቹ ዋቢዎቼ ዘንድ “ሴት አረደችኝ” የሚል ሲሆን በሌሎቹ ደግሞ “ሴት አረዳችው” የሚለው ተውኔቱ ነው። ይህም የታሪክ መዛባት ከላይ በጠቀስኩት ችግር ምክንያት የመጣ መሆኑን ልብ ይሏል። ከመጀመሪያው ተውኔቱ በኋላ በተከታታይ “ሰይጣን ለወዳጁ ቅርብ ነው”፣ “የክህደት ኑሮው መቅሰፍት”፣ “ዓርብ ጥላኝ ሄደች”፣ “ሽፍንፍን”፣ “ማሪኝ”፣ “ለኔ ብቻ”፣ “የትምወርቅ’ና እንዳሻው”፣ “አዬ ሰው”፣ እና “አንድ ጡት” የተሰኙ ተውኔቶችን ፅፎ ለመድረክ አብቅቷል።

እራሱን በራሱ ያስተማረው፣ ዘናጩ፣ የጥበብ ቀንዲል መላኩ አሻግሬ በ1962 ዓ.ም ተጓዥ ቴአትርን መስርቶ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ ስሙን በደማቁ የፃፈበትን ተግባር ፈፅሟል። ከማቲዎስ በቀለ የቴአትር ቡድን ቀጥሎ የተመሰረተው በሀገራችን ሁለተኛው የግል የቴአትር ቡድን መላው ኢትዮጵያን በመዞር የቴአትር ጥበብን አስተዋውቋል፣ አስተምሯል፣ አዝናንቷል፣ መዳፍን በአፍ ላይ አስጭኗል። በአዲስ አበባ ብቻ ታጥሮ ይኖር የነበረውን የቴአትር ጨዋታ ለሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች፤ ገጠራማ ቦታዎች ሳይቀር በማዳረስ ሙያዊ ግዴታውን እንከን የለሽ በሚያስብል ደረጃ ተወጥቷል።

ለእውነት ሟቹ፣ “በ’ኔ ፊት ደግማችሁ የማትሉትን ነገር አትናገሩ” ባዩ መላኩ በ1968 ዓ.ም ቡድኑ ሲፈርስ እንደገና ሀገር ፍቅርን በመቀላቀል እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ በሀገር ፍቅር ሰርቷል። የድንገቴ ፈጠራው ንጉስ መላኩ፣ ጥርስ አያስከድኔው ከያኒ ስለ ፍቅር፣ ጥላቻ፣ ህይወት፣ ጉቦ፣ ነፃነት፣ እኩልነት፣የገዢ መደቦች ጭቆና፣ እምነት፣ በነባሩና አዲሱ ትውልድ መካከል ያለውን የአስተሳሰብ ልዩነት፣ የህብረተሰቡን ችግር የሚዳስሱ ከ25 በላይ ተውኔቶችን ፅፏል። ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ፦ “ጊዜ”፣ “የለሁም በለው”፣ “አለም ጊዜ’ና ገንዘብ”፣ “ማጣት’ና ማግኘት”፣ “ምን አይነት መሬት ናት”፣ “የቆሰለች ስጋ”፣ “ጉድ ፈላ”፣ “ህልም ነው”፣ “ግንድ አልብስ”፣ “ሲጠነዛ”፣ “ይቅርታሽን”፣ “ነፍስ ይማር”፣ “ባቡር” (በሳንሱር ምክንያት የወደቀ)፣ “መጠረግያ ያለው”፣ “የእሳት እራት” ናቸው።

ቸር ይግጠመን!

Melaku Ashagrie

69 views0 comments
bottom of page